የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን- ተመራቂ ተማሪዎች

59

ድሬዳዋ፣ የካቲት 28/2013 (ኢዜአ) 6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲካሄድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ።

 "ሁሉም ዜጋ በፍቅርና በአንድነት ለሀገር ልማትና ሉአላዊነት በጋራ የሚቆምበት ምዕራፍ  ላይ እንገኛለን"

ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ  የዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂዎች አስታውቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት የዋንጫና የመዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዮሴፍ ውቤ እንደገለጸው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሁሉም ተቋማትና ዜጎች ድርሻ ወሳኝ ነው።

"የተማርነው ኃይልም ምርጫው ህጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡን በማስተባበርና በማሳወቅ የድርሻችንን እንወጣለን" ብሏል፡፡

ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3 ነጥብ 95 በማምጣት የተመረቀው ምንተስኖት ከበደ በበኩሉ የተማረው አካል ለምርጫው ስኬታማነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግሯል፡፡

ምርጫው የሀገሪቱ መጪ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዞ የሚወሰንበት ምዕራፍ በመሆኑ የተሻለ ሃሳብ ይዞ የመጣን ፓርቲ እንደሚመርጥ አመላክቷል።

"ምርጫው ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሆን የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ያለችው ደግሞ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የተመረቀችው በእምነት ይልቃል ናት፡፡

"በዘንድሮ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ ሴቶች በመምረጥ ላይ ያላቸው ተሣትፎ እንዲጎለብት አስተምራለሁ "ብላለች፡፡

የህግ ተመራቂው መሃመድ ሁሴን በበኩሉ "ምርጫው ነጻ ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ መደገፍ ለኛ ሀገር ገንቢና ተረካቢዎች መሠረታዊ  ነገር ነው " ብሏል።

"ወደ አካባቢዬ ስመለስ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን የሚጠበቅብኝን አበረክታሁ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግስትም ለምርጫው ተአማኒነት የድርሻቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል" ሲል ተናግሯል፡፡

 በማኔጅመንት ትምህርት የተመረቀው አራርሶ ቦጋለ ተምሮና ፊደል ቆጥሮ ሀገር መረበሽ የሚያስነውር ተግባር በመሆኑ የተማረው አካል ባልጠራ አሉባልታ ንጹሃንን ከመመረዝ እንዲታቀብ ጥሪ አቅርቧል፡፡

"ኢትዮጵያችን ከኛ የምትፈልገው በፍቅርና በአንድነት ሆነን በሀገር ሉአላዊነትና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተጋረጠን ችግር እንድንከላከል ነው" ብሏል፡፡

እንደ ምሩቃኑ ገለጻ ሁሉም ዜጋ ህብረትና አንድነቱን ጠብቆ የሀገሩን ህልውና የመጠበቅና የሚቃጣን የውጪ ኃይል ተንኮል የመመከት ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትላንት ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም