የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ የአገሪቷን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ማረጋገጥ ይገባል

123

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ) በተለያዩ መስኮች የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ የአገሪቷን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ከሴት ምሁራን ጋር መክሯል።

በምክክር መድረኩ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን የሚዳስስና በተለያዩ መስኮች ተሳትፏቸውን የሚያሳይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሪት ሃዳስ ኪዱ እንደገለጹት፤ ሴቶችን ያላሳተፈ ልማትና እድገት ውጤታማ አይሆንም።

ሴቶችን ወደ ሥራ ማስገባትና በተለያዩ የሙያ መስኮች ማሳተፍ በአገሪቷ ሁለንተናዊ ጥቅም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ሴቶች በራስ የመተማመን ብቃታቸው እንዲዳብርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውም እንዲረጋገጥ በትምህርት፣ በስልጠናና በመሳሰሉት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

"የሴቶችን መብት የሚያከብርና የሚያስከብር ማኅበረሰብ መፍጠርና መገንባትም የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል" ብለዋል የቢሮ ሃላፊዋ።

በመድረኩ የተሳተፉ ሴት ምሁራን በየደረጃው የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ በአገሪቷ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ጸዳለ ከበደ ሴቶች የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች በራሳቸው ተጋፍጠው በመወጣት 'አይችሉም' የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ከወንዶች እኩል ማግኘት የሚገባቸውን ውክልና ማግኘታቸውም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ለውጥ ማምጣት ያስችላል ብለዋል።

በፖለቲካው መስክ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ድርሻ በማሳደግ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

"ሴቶች በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ በመሆን ይችላሉ የሚለውን መንፈስ በሁሉም ዘንድ ማስረጽ ይገባቸዋል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የምክክሩ ተሳታፊ ወይዘሮ ፋሲካ ወርቁ ናቸው።

በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ያሉ ሴቶች ለሌሎች ሴቶች አርዓያነታቸውን በማስመስከር ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱ በማድረግ የራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ዘንድሮ ለ110ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም