የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ ተከናወነ

72

የካቲት 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ግንባታው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የተጀመረው የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ80 በመቶ በላይ መከናወኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የፓርኩ የግንባታ ሂደት በአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እንዳሉት፤ 59 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የተነሳ መጓተት አጋጥሞት ነበር።

ከመስከረም ወር ጀምሮ በተወሠደ የእርምት እርምጃ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ መከናወኑን ገልጸዋል።

በፓርኩ የማምረቻ ሼዶችንና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጨምሮ መሠረታዊ ግንባታዎች መገባደዳቸውን ጠቁመው፤ ቀሪው ስራ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የክልሉ አስተዳደርና ህዝብ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የለውጡ አመራር ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ የሰጠበት ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ሂደት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በቁርጠኝነትና ከተመሩ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚጠናቁ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከታጁራና ጀቡቲ ወደብን በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ተመራጭ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ፓርኩ በክልሉ እያደገ ለመጣው የስራ እድል ጥያቄ ምላሽ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ በመሳብ ብቁ የተማረ ሠው ሃይል ልማትና ተጓዳኝ ስራ እንደሚከናወን አቶ አወል አብራርተዋል።

የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቻይናው ሲ.ሲ.ሲ.ሲ. ኩባንያ ተቋራጭነት በ500 ሺህ ካሬ ሜትር ስኩየር መሬት ላይ እየተገነባ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም