የእምቦጭ አረምን በጨረር ማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች

71

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ)  በኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች የተዘጋጀውና የእምቦጭ አረምን በጨረር ማስወገድ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ በቤተ ሙከራ ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።

የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን በውሃ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ያዘጋጀው ጥናታዊ ሲምፖዚየም አዳማ ላይ እየተካሄደ ነው።

በሲምፖዚየሙ በተፋሰሶች ልማት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

በሲምፖዚየሙ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀረቡት ምሁራን የእምቦጭ አረም ከጣና በተጨማሪ በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሐይቆች ላይ በስፋት እየተከሰተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል የቆቃ እና ዝዋይ ሐይቆች ላይ ጥናት ያካሄዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ዶክተር አህመድ ሁሴን እምቦጭ አረም በሁለቱ ሐይቆች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያመጣ መሆኑን ይናገራሉ።

የዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ሰለሞን ለታ በበኩላቸው በቆቃ እና ዝዋይ ሐይቆች ባደረጉት ጥናት ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ለእምቦጭ አረም መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ ናይትሮጂን እና ፎስፈረስ የተሰኙ ንጥረ ነገሮች ለእምቦጭ አረም ተስማሚ ሆነው በመገኘታቸው አረሙ በፍጥነት እንዲስፋፋ እያደረጉ ስለመሆኑ በጥናት ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል።

እምቦጭ አረምን በጨረር ለማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ላይ ከባልደረቦቻቸው ጋር ጥናትና ምርምር እያካሄዱ የሚገኙት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ምህንድስና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ምህረት ዳናንቶ "ግኝቱ በቤተሙከራ ተፈትሾ ውጤታማ ሆኗል" ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ ከዚህ ቀደም እምቦጭ አረምን ለማስወገድ በእጅ የመንቀል፣ በማሽን የማጨድ፣ በኬሚካል የማከምና በነፍሳት የማስበላት ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲና ሃዋሳ ግብርና ኮሌጅ በጋራ እያካሄዱት ባለው በዚህ ጥናት የእምቦጭ አረምን በጨረር ማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ዶክተር ምህረት ቴክኖሎጂው ለሌሎች ብዝሃ ህይወት ጠንቅ ሳይሆን አረሙን ብቻ ለይቶ በጨረር ቴክኖሎጂ አማካኝነት ማስወገድ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።

ምርምራቸው በቤተሙከራ ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለና ስራውን ወደ መሬት ማውረድ እንዲቻል መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ የእምቦጭ አረምን መስፋፋት መግታትና አረሙን ማስወገድ የአገሪቷን የውሃ ሀብቶች በአግባቡ መጠበቅ እንደሚያስቻልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም