መስቀል አደባባይ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ላይ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

102
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ስራዎች ለመደገፍና እውቅና ለመስጠት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የፀጥታ አባላትና ግለሰቦች ላይ ፖሊስ የመጨረሻ የጊዜ ቀጠሮ ጠየቀባቸው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩትን ግርማ ካሳን ጨምሮ "ኃላፊነታችሁን በአግባቡ አልተወጣችሁም" በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የፌዴራል ፖሊስ አባላትና ግለሰቦች ዛሬ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሦስተኛ ጊዜ ቀርበዋል። የመርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ተጨማሪ ሰነዶችን ለመሰብሰብ፣ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝና የምርመራ ውጤቱንም አጠናቅሮ ለማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው በበኩላቸው ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተገቢነት እንደሌለው የተከራከሩ ሲሆን ምርመራው እየተጓተተ በመሆኑ የተጠየቀው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ እንዲሆን ተቃውሞ አቅርበዋል። በተጨማሪም ሕገ መንግስታዊ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። መርማሪ ቡድኑ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ ቢለቀቁ በሰውና በሰነድ የምርመራ ሥራ ላይ ተዕፅኖ ያሳድራሉ በማለት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል። ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በቀድሞው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳና በፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ አጠናቆ ለሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም የክስ መዝገብ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተጨማሪም በቦንብ ፍንዳታው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉ ግለሰቦች ላይም ፖሊስ ከጠየቀው አስር ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት ብቻ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።   በሌላ በኩል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የሥራ ኃላፊ የሆኑት በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ እና ሌላ አንድ ግለሰብ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን 12 የምርመራ ቀናት ችሎቱ ፈቅዷል።   መርማሪ ቡድኑ ሐምሌ 24፣ 27 እና ነሐሴ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም