በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ጊዜ ሠሌዳን መሠረት በማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው

61

አሶሳ፤ የካቲት 27 / 2013 (ኢዜአ) ፡- መተከል ዞንን ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫን ለማሳካት በጊዜ ሰሌዳው መሠረት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡

የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ታደሠ ለማ እንዳሉት በክልሉ 22 የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቶች በሰው ሃይል እና ቁሳቁስ ተደራጅተው  የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ተከትሎ ስራ ጀምረዋል፡፡

በጊዜ ሰለዳው መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች መዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ በተለይ በመተከል ዞን ምርጫ ክልሎች ተከፍተው ስራ ከጀመሩ አንስቶ ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ሃላፊው ጠቁመው ስራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የምርጫ ዝግጅት ከተጀመረ አንስቶ የመንግስት ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው የመተከል ዞን ጸጥታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ብለዋል፡፡

መተከልን ጨምሮ በክልሉ ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር እንደሚከናወን እምነታቸው መሆኑን  አቶ ታደሠ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል፡፡

በክልሉ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊና ክልላዊ  ምርጫ እንደሚወዳደሩ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እስካሁን የጋራ ምክር ቤቱን የሚመሩ አመራሮችን ጨምሮ በተያያዥ የምርጫ ጉዳዮች ተወያይተው እንደማያውቁ ጠቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገናኝተው ምክር ቤቱን ስራ እንዲያስጀምሩ አስገንዝበዋል፡፡

ቅርንጫፉም ምክር ቤቱን በማጠናክር የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ቦጋለ በበኩላቸው በክልሉ የምክር ቤቱ አባላት ያለመገናኘት ክፍተት ምክር ቤቱን እንዳይጠናከር አድርጎታል ብለዋል፡፡

አንዳንዶቹም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከሃላፊነት መልቀቃቸው ሌላው የምክር ቤቱ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በምርጫው የሚያከናውናቸው ተግባራትን የያዘ ዝርዝር እቅድ ማሰናዳቱን  ጠቁመው ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመቀናጀት የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ደንብ መሠረት በማድረግ በቅርቡ እንደገና ለማጠናከር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ለእቅዱ ማስፈጸሚያ የሚውል የበጀት ጥያቄ ለክልሉ መንግስት መቅረቡን አቶ ደሳለኝ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም