የብድር፣ የመስሪያ ቦታና መሰል ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሴት ነጋዴዎች ጠየቁ

70

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2013 ( ኢዜአ) የንግድ ሥራቸውን ለማስፋት የብድር፣ የመስሪያ ቦታና ተያያዥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሴት ነጋዴዎች ጠየቁ።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረውን  የሴቶች ቀን አስመልክቶ በከተማዋ እየሰሩ ካሉ ሴት ነጋዴዎችና ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።

የዘንድሮ የሴቶች ቀን  "የሴቶችን መብት የሚያስከብር ማህበረሰብ እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ መከበር የተጀመረ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ቀኑን አስመልክቶ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል

ከአባታቸው ባገኙት ወረት የንግድ ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሙሉጎጃም አባተ፣ በተለያዩ ጊዜያት የመኪና መለዋወጫ ማቅረብ፣ የፅህፈት መሳሪያዎችን መሸጥና ሌሎች ሥራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅትም ጨው በማምረት ሥራ ላይ መሰማራታቸውንና ካፒታላቸውም 40 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገልፀዋል።

በተበደሩት አምስት ሺህ ብር መነሻነት ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ ጀምረው አሁን ላይ ካፒታላቸው 80 ሺህ ብር መድረሱን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አበባሽ ክፍሌ ናቸው።

በምግብ ዝግጅት ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ አበባሽ፣ ከራሳቸው አልፈው ሦስት ሴቶችን ቀጥረው እያሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ከብድርና የመስሪያ ቦታ እጥረት ጋር በተያያዘ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

በሥራ ሂደት የገጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እየሰሩ ቢሆንም የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ይህ ተግባር መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይ የንግድ ሥራቸውን ለማስፋት የገንዘብ ብድር፣ የመስሪያ ቦታና ተያያዥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የጠየቁት።

ሴቶች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ራሳቸውን ማብቃትና ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን አህመድ እንዳሉት ቢሮው በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

"የሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት በሌላው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ቢሮው እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ሥራ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሴቶች የሚገጥማቸውን የመስሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስስርና ከብድር ጋር የተያያዙ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።

የቅንጅት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ።

እንደ ወይዘሮ ብርቱካን ገለጻ፣ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ተመርቀው ወደስራ ያልገቡ ከአምስት ሺህ በላይ ሴቶችን በመለየት ምርጫን በማገዝ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ትስስር ተፈጥሯል።

"ወደ አመራርነት መምጣት የሚችሉ 238 ሴቶችንም በመለየት ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በተያዘው ዓመት 40 አካልጉዳተኛ ሴቶች የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም ምክትል ኃላፊዋ አመልክተዋል።

የመስሪያ እቃዎችን በማጣት ሥራ ላልጀመሩ ሴቶች  3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልፀው፤ በዚህም ስልጠና ያገኙ አካል ጉዳተኛ ሴቶችን ጨምሮ ለ1 ሺህ 140 ሴቶች የመስሪያ እቃ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም