ተቋማት፣ የመንግስት ሠራተኞችና ነዋሪዎች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

112
ደብረብረሀን/ፍቼ  ሀምሌ 20/2010 በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ተቋማት፣ የመንግስት ሠራተኞችና ነዋሪዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ ። የደብረብሃን ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በኢንጅነር ሰመኘው ህለፈተ ህይወት የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ አስተዳደር ሠራተኞችና መምሀራን ማዘናቸውን ገልጿል ። ዩኒቨርሲቲው ኢንጅነሩ የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ምልክት የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በብቃት በመምራት ለፈፀሙት አኩሪ ተግባር አድናቆትና እውቅና መስጠቱን በመግለጫው አስታውቋል ። ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል። የአጎለላና ጠራ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትም ኢንጂነር ሰመኘው አገሪቱ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን ራዕይ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የጎላ ድርሻ እንደነበራቸው አስታውቋል። በተለይ በህዝብ ሀብት የተጀመረውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  በብቃት የመሩ መሆናቸውን ለኢዜአ በላከው በመግጫ አስታውቅል። "ኢንጅነሩ በህይወት ቢለዩንም የወረዳው ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከዳር ለማድረስ በገባው ቃል መሰረት ተሳትፎውን አጠናክሮ ይቀጥላል" ያለው ጽህፈት ቤቱ፣ በደረሰው ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጾ ለቤተሰቦቸቸው መጽናናትን ተመኝቷል። በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞንና የፍቼ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎችም  በኢንጂነር ሰመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል። የዞኑና የከተማው አገር ሽማግሌዎና ነዋሪዎች እንዳሉት ኢንጅነሩ ለአገራቸው ልማትና እድገት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በበርሃ ለአገር መስዋዕትነት የከፈሉ ታላቅ ሰው ነበሩ ። የኢንጅነሩ ሞት አስደንጋጭና አሳዛኝ እንደሆነባቸው በመግለጽ በኢንጀነር ስመኘው ሥራ አስኪያጅነት ተጀምሮ የተጋመሰው የህዳሴ ግድብ  ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። የፍቼ ከተማ መምህራን ማህበር በበኩሉ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ ኢንጅነሩ ለአገሪቱ እድገትና ልማት ሲያበረክቱት የነበረው የጎላ አስተዋጽኦ ከግብ እንዲደርስ ማህበሩ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ  አስታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም