የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ማሳያ ነው -የኪነጥበብ ባለሙያዎች

81

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2013 ( ኢዜአ) የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ማሳያ ነው ሲሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ገለፁ።

በጥበቡ ዓለም ሰዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ሥራቸው ለህዝብ ሲደርስ በአድማጮቻቸውና ተመልካቾቻቸው ዘንድ “መቼ ሰርቶት ነው?” የሚል ጥያቄ ሊያስነሳና የመነጋገሪያ ርዕስም ሊሆን ይችላል።


የጥላሁን ገሠሠ አዲሱ “ቆሜ ልመርቅሽ” አልበምም የአልበሙን ሥራ ሲያከናውኑ ከነበሩት የኪነጥበብ ሰዎች በስተቀር አልበሙ ለህዝብ ጆሮ እንደሚበቃ ስለማይታወቅ ብዙዎችን ሊያነጋግር ይችላል።


ከሙዚቃ አልበሙ መመረቅ በኋላ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኪነጥብ ባለሙያዎች እንደገለፁት የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ መውጣት ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት የራሱን አሻራ ያሳርፋል።


የጥላሁን ገሠሠን የአልበም ሂደት ሲከታተል የነበረው አርቲስት አበበ ባልቻ የጥላሁን ገሠሠ አልበም መመረቅ ዋና ዓላማ ለስሙ የሚመጥን አሻራ ለመተው መሆኑን ይገልጻል።


“የጥላሁን ሙዚቃ ማለት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ሂደት አንዱ ማሳያ ነው” ሲልም ተናግሯል።


የሙዚቃ ሥራዎቹ በብዙ ውጣ ውረድ አልፈው የመጡ በመሆናቸው ለኅብረተሰቡ አስተማሪ መሆናቸውንም ነው የገለጸው።

"በተለይ የአገር ፍቅርን አጉልቶ ማንሳቱና ስላለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ መልካም ምኞቱን በሙዚቃው መግለፁ ጥላሁንን ልዩ ያደርገዋል" ብሏል።

አልበሙ ተዘጋጅቶ እንዲወጣ ከመንግስት፣ ከከተማ አስተዳደሩና ከሙያ አጋሮቹ የተደረገው ድጋፍም የጥላሁን ሥራ በአገሪቱ ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን ነው አርቲስቱ የገለጸው።


በአልበሙ የግጥም ሥራ ላይ የተሳተፈው ያየህይራድ አላምረው የቀረቡት ሙዚቃዎች ጥላሁን ደጋግሞ ካቀዳቸው የተመረጡ መሆኑን ገልፆ፣ ለሙዚቃው ዕድገት የራሳቸው ድርሻ  እንደሚኖራቸው ተናግሯል።

የሙዚቃ አቀናባሪው አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ በበኩሉ "አልበሙ ተሰርቶ በጅምር አለመቅረቱ የሌሎችንም በሕይወት የሌሉ ሙዚቀኞች ሥራዎችን እንድንፈትሽ ያነሳሳል" ብሏል።


ጥላሁን ገሠሠ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ከላይ የተሰጠ ስጦታ መሆኑንና ለሙዚቃው ዘርፍ ትልቅ ሚና ሲጫወት እንደነበረ የገለጸችው ደግሞ አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ ናት።


የጥላሁን ገሠሠ “ቆሜ ልመርቅሽ” ሙሉ የሙዚቃ አልበም ለዳግማይ ትንሣኤ ከሙዚቃ ኮንሰርት ጋር እንደሚለቀቅ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም