ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአምስት አገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

81

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2013 ( ኢዜአ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የአምስት አገራት አዳዲስ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት የአምስቱ አገራት አምባሳደሮች የአሜሪካ አምሳደር ጌታ ፓሲ፣ የኬንያ አምባሳደር ጀኤን ካማዑ፣ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ታማራ ሞና፣ የቻድ አምባሳደር መሃማት አሊ ሃሰን እና የጋምቢያ አምባሳደር ከኒናባ ጃኜ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅም የተሿሚዎችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል፤ ከአምባሳደሮችም ጋር በኢትዮጵያና አገራቱ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት አገራቸውን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም ለአምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ከትግራይ የህግ ማስከበር ተልዕኮ በኋላ ስላለው ሰብዓዊ አቅርቦት ለአምባሳደሮቹ ማስረዳታቸውንም ተናግረዋል።

አምባሳደሮቹም ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን በተለይም የአፍሪካ አገራት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ በኩል በቅርበት ለመስራት መስማማታቸውን አንስተዋል።

በተለይም ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በአሜሪካ በኩል ለተነሱ ጉዳዮች ፕሬዚዳንቷ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

"በዚህም የሰሜን ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ መብት መከበር ጠንካራ አቋም እንዳለው ገልጸውላቸዋል ነው" ያሉት።

መንግስትም ሰብዓዊ ርዳታ እያደረሰ መሆኑንና ሌሎች ድጋፎችም እንደሚያስፈልጉ ገልጾላቸዋል፤ የአሜሪካ አምባሳደርም ለሰብዓዊ እርዳታው ድጋፍ ለማድረግ እንደሚፈልጉም መግለጻቸውን ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም