ለኢንዱስትሪው ጉዞ የሳይንስ ባለሙያዎችንና ሳይንቲስቶችን ይዞ በፍጥነት መንቀሳቀስ ይገባል-ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ

71
አዲስ አበባ  ሀምሌ 20/2010 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አገሪቷ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለምታደርገው ጉዞ  የሳይንስ ባለሙያዎችንና ሳይንቲስቶችን ይዞ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝዳንቱ የሳይንስ ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተገኝተው ጎብኝተዋል። ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አገሪቷ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለምታደርገው ርብርብ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሳይንስ ባለሙያዎችንና ሳይንቲስቶችን ይዞ የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል። አገሪቷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ወደ ኋላ መቅረቷ ኋላ ቀር ቴክኖሎጂና እድገት እንዲኖራት ማድረጉን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ችግሩን  ለመቅረፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሳይንስ ባለሙያዎችና ሳይንቲስቶችን አቅምን አብዝቶ መጠቀም ይገባዋል። በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ የሚያስመርቋቸውን የመጀመሪያ፣ የሁለተኛና የሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎችና ተመራማሪዎችን አቀናጅቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል። ይህም አገሪቷ ያላትን ትልቅ የሰው ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል ብለዋል። ሚኒስቴሩም የአገሪቷን እድገት ለማፋጠን የቀረጻቸው ፕሮጀክቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው እነዚህን ፕሮጀክቶች በሙከራ ደረጃ ወደ ተግባር አስገብቶ ውጤታቸውን እየገመገመ በመላው አገሪቷ ማስፋፋት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው አገሪቷ እስካሁን ቴክኖሎጂን ማዕከል ያላደረገ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች መምሯቷ እድገቷ እንዲዘገይ አድርጓል። በመሆኑም የአገሪቷን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የጤና፣ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በሚኒስቴሩ ተጀምረው እየተተገበሩ ይገኛሉ ብለዋል። በወጣቶች ማዕከል የሚተገበረው የሳይንስ ካፌ፣ የቡራዩ የተሰጥኦና የፈጠራ ትምህርት ቤት ማዕከል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግንባታ ማዕከል፣ የእንስሳት ሃብትን ለማሻሻል የሚያስችል ቴክኖሎጂና ዘመናዊ ማረሻ ሥራ ከፕሮጀክቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለአንድ አገር የማደግና ያለማደግ አለም አቀፍ መመዘኛ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገሪቷን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማህበራዊ አኗኗርና ግብር አሰባሰብ ለማዘመንና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ያስችላሉ። ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶቹን በ2011 ዓ.ም ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም