የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና መሪው ፓርቲ አብዴፓ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

56
ሰመራ ሃምሌ 20/2010 የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና መሪው ፓርቲ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ። የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ አብዱሶመድ መሀመድ እንዳሉት ኢንጅነር ስመኘሁ በቀለ አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን ልማት ከግብ ለማድረስ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ አገር ወዳድና ተታሪ ሰው ነበሩ። በተለይም የአገሪቱ በራስ የመልማት ውጥን ከዳር እንዲደርስ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በሌሎች መሰል ሥራዎች ላይ አርአያነት ያለው ተግባር በመፈጸም ኃላፊነታቸውን በብቃት የተወጡ ታላቅ ሰው መሆናቸውን አመልክተዋል። በመሆኑም የክልሉ መንግስትና ህዝብ በኢንጂነር ስመኘሁ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግብ እንዲደርስ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። "የክልሉ መንግስት ለኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦችና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል" ብለዋል። በተመሳሳይ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ አብደላ በበኩላቸው ኢንጅነር ስመኘሁ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ታልቅ አገራዊ አደራ ለመወጣት ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለችኝ ሳይሉ ሲሰሩ የነበሩ የልማት ጀግና መሆናቸውን ገልጿል። ኢንጂነር ስመኘሁ አገሪቱ የኃይል ፍላጎቷን ለማርካት ባደረገችው ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ብቃታቸውን በተግባር አሳይተዋል። በላፉት ሰባት ዓመታት የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የነበረውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ በግንባር ቀደምነት በመምራት በህዝቡ ውስጥ የነበረውን የአይቻልም ስሜት በማስወገድ ህዝባዊ መነቃቃትና መነሳሳት የፈጠሩ ሰው መጎናቸውንም ፓርቲው አስታውቋል። ከእዚህ በተጨማሪ በየጊዜው ለሚዲያና ለሕብረተሰቡ ስለግድቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት የህብረሰቡን ድጋፍ ሲያቀጣጥሉ እንደነበር አስታውሷል። በመሆኑም ህዝቡ ለሕዳሴ ግድቡ ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ የበለጠ በማጠናከር የኢንጂር ስመኘው ልፍትና ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ፓርቲው  ከክልሉ መንግስትና ህዝብ ጋር በመሆን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አመልክተዋል። የፌዴራል መንግስትም የኢንጂነሩን ሞት ምክንያት በሚገባ አጣርቶ እውነታውን ለህዝብ ለማሳወቅ በሚያደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ሁሉ መሪ ፓርቲ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም