አገር አቀፍ የኤች.አይ.ቪ መቆጣጠሪያና ምላሽ መስጫ መመሪያ ይፋ ሆነ

78

የካቲት 25 / 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኤች.አይ.ቪ ቅኝት መረጃ መሠረት በጣም ተጋላጭ በሆኑ የኅብተረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚተገበር አገር አቀፍ መቆጣጠሪያና ምላሽ መስጫ መመሪያ ይፋ አደረገ።

የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ የሆነው መመሪያው በጣም ተጋላጭ ተብለው በግኝት በተለዩ 313 ወረዳዎች ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

የ'ኤች.አይ.ቪ ቅኝት' ማለት የየኤች.አይ.ቪ ጫና መሠረት ተደርጎ በመደበኛነት ከጤና ተቋማት የሚሰበሰብ መረጃ ነው። 

ኢንስቲትዩቱ ከ2010 ዓ.ም እስካሁን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙትን መሠረት በማድረግ በተመረጡ 613 ጤና ተቋማት ላይ ጥናት በማድረግ 15 ሺህ 600 የኅብረተሰብ ክፍሎች መመርመሩን አስታውቋል።

በኢንስቲትዩቱ የኤች.አይ.ቪ እና ቲቢ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክተር አቶ ይማም ጌታነህ እንዳሉት በተሰበሰበው መረጃ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ፣ ክትትልና መድሃኒት ማስጀመር የሚሉ የመረጃ ግብዓቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ግኝቱ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ፣ ተማሪዎች፣ ስራ የሌላቸውና የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች ለየኤች.አይ.ቪ በጣም ተጋላጭ መሆናቸውን አመላክቷል ብለዋል። 

በግብዓቶቹ ላይ መሠረት ያደረገና መረጃ ላይ የተመሰረተ የየኤች.አይ.ቪ ጤና አገልግሎት በመስጠት አገር አቀፍ ምላሽ መስጫ መመሪያው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

መመሪያው በጣም ተጋላጭ የሆኑት የኅብተረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን የየኤች.አይ.ቪ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በትኩረትና በሰፊው ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን ክልሎች በራሳቸው የየኤች.አይ.ቪ ቅኝት መረጃ መሠረት እንደየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ እንዲሰሩ ድጋፍ ይደረጋል ያሉት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የየኤች.አይ.ቪ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ምርቴ ጌታቸው ናቸው። 

ዓላማውም በውጤቶች መሰረት ምላሽ መስጠትና ወረርሽኙን መቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች በመከወን የየኤች.አይ.ቪ ስርጭት አሁን ካለበት በብዛት ቀንሶ በ2030 ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ነው ብለዋል።

መመሪያው በጣም ተጋላጭ የኅብተረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች በመለየት የደም ምርመራና በደም ውስጥ ያለን የቫይረስ ምጣኔ ዝቅተኛ በማድረግ ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 

አገራዊ የየኤች.አይ.ቪ ስርጭት ከክልል ክልል የተለያየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ዝቅተኛው ሶማሌ ክልል ዜሮ ነጥብ 15 በመቶ እና ከፍተኛው ደግሞ ጋምቤላ 4 በመቶ ይደርሳል ነው የተባለው።  

አገራዊ የስርጭት መጠን ምጣኔው ዜሮ ነጥብ 9 በመቶ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም