በንብረት አያያዝና አስተዳደር ችግር በቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ለብክነት እየተዳረገ ነው

48

የካቲት 25 / 2013 (ኢዜአ) በንብረት አያያዝና አስተዳደር ችግር ምክንያት በቢሊዮኖች ብር የሚቆጠር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ለብክነት እየተዳረገ መሆኑ ተገለጸ።

የፌደራል ተቋማት ከሚመደብላቸው ዓመታዊ በጀት ከ65 በመቶ በላይ የሚጠቀሙት ለንብረት ግዢ እንደሆነ ተመልክቷል።

የመንግስት የግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ "ግዢን በእቅድ በመምራት የንብረት አስተዳደርን ውጤማነት ማሳደግ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ የፌደራል ተቋማት በእቅድ የተመራ ግዢ ማከናወንና የገዙትን ንብረት በአግባቡ መጠበቅና ማስተዳደር እንደሚገባቸው በአዋጅ መደንገጉን ገልጸዋል።

ይሁንና ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ንብረቶች ለብክነት እየተዳረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ንብረቶች ያለጥቅም ረጅም ጊዜ በመቀመጣቸው ለብልሽት እንደሚዳረጉ ገልጸው፤ ንብረቶች ተጠግነው ድጋሚ ስራ ላይ እንዲውሉ የማድረግ ባህል ተቋማት እንደሌላቸው ጠቅሰዋል።

ብክነቱን በቁጥር ለመግለጽ ጥናት የሚፈልግ መሆኑን ተናግረው፤ "በአሁኑ ሰዓት መንግስት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣባቸው ንብረቶች እየባከኑ መሆናቸውን በግልጽ መናገር ይቻላል" ብለዋል።

ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።ችግሩን ለመፍታት በቀጣይ በንብረት አስተዳደር የሚሰጡ አስተያየቶችን መሰረት አድርገው በማይሰሩ የፌደራል ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ዶክተር ኢዮብ አመልክተዋል።

የመንግስት የግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በበኩላቸው ለግዢና ንብረት አስተደዳር ማነቆ የሆነውን በማሻሻል ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በየተቋማቱ ለሚገኙ ንብረትና ግዢ ክፍሎች የሚሰጠውን አነስተኛ ትኩረት ለመለወጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በእቅድ ያልተመሩ ግዢዎችና ንብረቶች ለማስወገድ ያለው ሂደት ጊዜ መውሰድ የብክነቱ መንስኤ እንደሆኑ ገልጸው፤ የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፌዴራል ተቋማት ከሚመደብላቸው ዓመታዊ በጀት ከ65 በመቶ በላይ የሚጠቀሙት ለንብረት ግዢ እንደሚጠቀሙ የመንግስት የግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም