በሲዳማ ክልል ህዝቡን ያሳተፈ የሙስና ለመከላከል የሚያግዝ ሥልጠና ለሩብ ሚሊዮን ዜጎች ተሰጠ

53

ሀዋሳ ፤ የካቲት 25/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ህዝቡን ያሳተፈ የተቀናጀ የሙስና ለመከላከል የሚያግዝ ሥልጠና ለሩብ ሚሊዮን ዜጎች መስጠቱን የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ሥልጠናው የተሰጠው በሙስና ምንነትና መከላከያ ስልቶች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመልክቷል።

የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ስጦታው ወንጫኖ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት አራት ወራት የተሰጠው ይሄው ሥልጠና  በየደረጃው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።

የፀረ-ሙስና ትግሉን ለማጠናከር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሥልጠና ከተሰጣቸው መካከል 39 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች ይገኙበታል።

ሥልጠናውን ለማካሄድ በሲዳሚኛ ቋንቋ የሥነ ምግባር ደንብ፣ የፀረ-ሙስና ህጎችና ስልቶች ላይ ያተኮረ  አምስት "ሞጁል" በማዘጋጀት  መፈጸም መቻሉን አስረድተዋል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ ሙስናና ብልሹ አሠራር ትልቁ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ግንባታ እንቅፋት ከመሆን ባለፈ ለተገልጋይ ህብረተሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳይገኝ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

እንዲሁም ለልማት ስራ የሚመደበው የመንግስትና ህዝብ  ሀብት  በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል እያደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በዋናነት በመልካም ሥነ-ምግባርና በሙስና አስከፊነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት ለማከናወን ኮሚሽኑ  እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጓዳኝም ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ አሠራሮችን በጥናት በመለየት መፍትሄዎችን ፈልጎ ተግባራዊ  ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሙስናን ለመከላከል የሚደረገው ትግል ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው ከሚገኙ አመራር አካላት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ስጦታው ይህንን እውን ለማድረግ በስነ ምግባርና ሀብት የማሳወቅና ማስመዝገብ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከክልል እስከ ወረዳ ለሚገኙ 427 ተሿሚዎችና አመራሮች መስጠቱን አብራርተዋል።

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ  ግብርና ቢሮ ሰራተኛ አቶ በቸና ጎሶማ በሰጡት አስተያያት ሥልጠናው በሙስና ፅንፀ- ሃሳብና በተቀናጀ ተቋማዊ መከላከል ስትራቴጂ ላይ ግንዛቤያቸውን እንዳሳደገላቸው ተናግረዋል።

በቀጣይ በተቋማቸው ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን  ለመወጣት እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም