የደምበጫ-ሰከላ እና ቢቡኝ ወረዳ የመንገድ ግንባታ የ40 ዓመታት ጥያቄ መልስ ነው...የአካባቢው ነዋሪዎች

214

የካቲት 25/2013(ኢዜአ) መንግስት አያቶቻችን ከ40 ዓመት በላይ ሲያነሱት የቆዩትን ጥያቄ ለመመለስ የጀመረው የመንገድ ግንባታ አስደስቶናል ሲሉ በአማራ ክልል የደምበጫ-ሰከላ ፈረስ ቤት ነዋሪዎች ተናገሩ።

በአማራ ክልል የደምበጫ-ሰከላ እና ቢቡኝ ወረዳ 70 ኪሎ ሜትር አገናኝ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀምሯል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በመንገድ እጦት ምክንያት ወላድ እናቶች፣ አዛውንትና ሕሙማንን ፈጥኖ ወደ ሕክምና ማድረስ የማይቻል በመሆኑ የበርካቶች ሕይወት አልፏል።

ነዋሪው መንገድ እንዲገነባለት ከ40 ዓመት በላይ ሲጠይቅ የቆየ ቢሆንም ምላሽ ሳያገኝ በችግር ማሳለፉንም ነው የገለጹት።

መንግስት በመደበው ከፍተኛ በጀት የደምበጫ-ሰከላ እና ቢቡኝ መንገድ ግንባታ መጀመር በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በደጋ ዳሞት ወረዳ የፈረስ ቤት ቀበሌ ነዋሪው አቶ አለሙ ዘለቀ የአካባቢ ነዋሪ መንገዱ የተስተካከለ ባለመሆኑ ለማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርጎ መቆየቱን ገልፀዋል።

በመንገዱ ምቹ አለመሆን ሳቢያ ወደ አካባቢው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች በሚያጋጥማቸው ተደጋጋሚ የመገልበጥ አደጋ የአዛውንቶች፣ የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችና እናቶች ሕይወት መጥፋቱን አውስተዋል።

በደጋ ዳሞት ወረዳ ከ64 ዓመት በላይ መኖራቸውን የገለጹት ቄስ ወርቄ በላይነህም የአካባቢው ሕዝብ በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ በርካታ እንግልቶች ይደርሱበታል ነው ያሉት።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወንግስት ኤሌክትሪክ፣ ትምሕርት ቤትና የመንገድ ግንባታዎችን በማስጀመር  አካባቢው እንዲለማ በማድረጉ የአካባቢው ነዋሪ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ችሏል ብለዋል።

እንዲህ አይነት አሰቃቂና ለኑሮ ምቹ ያልሆነ ቦታ ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም የያለችው ደግሞ መምሕርት ሀገሬ አስማማው ነች።

በመንገዱ ምቾት አልባነት በርካታ አሰቃቂ አደጋዎች ሲደርሱ መመልከቷን ገልፃ ግንባታው መጀመሩ ለሕዝቡ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ገልፃለች።

መምህርቷ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ ተጠናቆ የተሻለ ኑሮና የመሰረተ ልማት እንደሚኖር እምነቷን ገልጻለች።

በመንግስት በተመደበ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ግንባታው የተጀመረው በምዕራብ ጎጃም ዞን የደምበጫ-ሰከላ እና ቢቡኝ ወረዳ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በሶስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም