የጎንደር ከተማ ሰልፍ ሰላምን በማይሹ ኃይሎች ዓላማውን እንዳይስት ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስተዳደሩ አሳሰበ

97
ጎንደር ሀምሌ 20/2010 የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ለመግለጽ እያካሄደ ያለው ሰልፍ ሰላምን በማይሹ ኃይሎች ዓላማውን እንዳይስት ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የከተማዋ አስተዳደር አሳሰበ፡፡ በሺዎች  የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ዛሬ በከተማው አደባባዮች በኢንጂነሩ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን  በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር የጸጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ዘለቀ አለባቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ጥልቅ  ሀዘን ተሰምቶታል፡፡ " ህዝቡ በኢንጂነሩ ድንገተኛ ሞት  ከትናንት ምሽት ጀምሮ ሀዘኑን እየገለጸ ነው"  ያሉት ኮሎኔሉ ዛሬም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሀዘኑን ሲገልጽ ማርፈዱን ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሉ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ሰልፉ ወደ አላስፈላጊ ግጭትና ብጥብጥ እንዳያመራ ጥረት መደረጉን ጠቁመው የወጣቱ ተሳትፎና ድርሻም ከፍተኛ እንደነበረም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ህዝቡና ወጣቱ በኢንጂነሩ ሞት የተሰማውን ሀዘን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ የቻለ ሲሆን በንብረት ላይም ጉዳት እንዳይደርስ ህዝቡና ወጣቱ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን ተናግረዋል፡፡ ሰልፉ ሰላምን በማይሹ ኃይሎች ዓላማውን እንዳይስት ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡ ትናንትም  በከተማው በበካፋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ በብልሽት ቆሞ የነበረ አውቶብስ የቃጠሎ ጉዳት እንደደረሰበት ተመልክቷል፡፡ ከሰልፉ ተካፋዮች መካከል ከማራኪ ክፍለ ከተማ የመጣው ወጣት መልካም ቁምልኝ በሰጠው አስተያት የሀገር ባለውለታ በሆኑት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማው ሀዘን  ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከኮሌጅ አካባቢ እንደመጣ የሚናገረው ወጣት እያቸው ወርቁ በበኩሉ "በሰልፉ ላይ የተገኘሁት በኢንጂነሩ ሞት የተሰማኝን ሀዘን ለመግለጽ፣ መደመር የማይፈልጉ አካላትን ለማውገዝና ለህግ እንዲቀርቡ ድምጼን ለማሰማት ነው "ብሏል፡፡ "የኢንጅነሩ ግድያ ትውልድ ገዳይ የፈሪዎች በትር ነው ሲሉ የተናገሩት ደግሞ በጎንደር የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ጡረተኛ አድማስ ደሞዜ ናቸው፡፡ የከተማዋ ህዝብ በሀዘን ድባብ ውስጥ ቢሆንም ቁጣና ብስጭቱን በትእግስት ይዞ የከተማዋ ሰላም እንዲደፈርስ ከሚሹ ኃይሎች አጥብቆ ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ እንጅነር ስመኘው በቀለ ትናንት  አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው አልፎ እንደተገኙ ይታወቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም