በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

68
ጅማ/መቱ/ጎባ/ጊምቢ/ጭሮ ሃምሌ 20/2010 በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ ። ሐዘናቸውን የገለፁት በጅማ፣ ጎባ፣ መቱ፣ ጊምቢና ጭሮ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ናቸው ። የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት የአገር ጀግና የሆኑትን ኢንጅነር ስመኘው በሞት ቢያጧቸውም የተጀመረውን ግዙፍ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር በማድረስ የደከሙበትን ለፍሬ ለማብቃት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የጎባ ከተማ ነዋሪዎችም ኢንጂነሩ አገሪቷ በሁሉም መስክ ተለውጣ ለማየት የነበራቸው ብሩህ ተስፋ እንዳይጨልም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ደጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት ። የመቱና ጎሬ ከተሞች ነዋሪዎችም ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ለራሳቸው ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ኖረው ያለፉ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል። ኢንጂነር ስመኘው የሕዳሴውን ግድብ እውን ለማድረግ ሲታትሩ የቆዩ የአገሪቱ ታላቅ ሰውና ባለውለታ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጊምቢና ጭሮ ከተሞች ነዋሪዎች ናቸው። ነዋሪዎቹ በኢንጅነሩ ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል። የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ለዓመታት የደከሙበትን ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ ለኢንጅነሩ ቤተሰቦችና የቅርብ ጓደኞች መጽናናትን ተመኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም