ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ምንጩን ማድረቅ ላይ ሊሰራ ይገባል - አቶ ደመቀ መኮንን

68

የካቲት 24/2013 (ኢዜአ) ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ምንጩን ማድረቅ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ኢትዮጵያ በነጻነት የአፍሪካ ኩራት ብትሆንም ይህ በጎ ገጽታዋ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እየተሸፈነ ነው ብለዋል።
በሰው የመነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የሚያግዝ ብሔራዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።  

ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለተለያዩ ጥቃቶች የተዳረጉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።  

ለዚህም ሰፊ የስራ አጥ ቁጥር መኖር፣ ከድላላ ስራው የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ መሆን እና ድህነት መንስኤዎች መሆናቸው በመድረኩ በቀረበው የውይይት መነሻ ጸሁፍ ተገልጿል።

በህጋዊ ሽፋን ህገ ወጥ ስራ የሚሰሩ አሰሪና ሠራተኛ አገናኝ መኖራቸው ሌላው የተነሳ ችግር ሲሆን ህግ የማስከበሩ ሂደትም ክፍተት እንዳለበት ተመላክቷል።  

እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመከላከል ለአምስት ዓመት የሚቆይ የድርጊት መርሃ ግብር በንቅናቄ መድረኩ ላይ ይፋ ሆኗል።   

መርሃ ግብሩ በሚተገበርባቸው ጊዜያት 20 ሺህ ቀበሌዎችን በመረጃ ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት እንደሚሰራም ነው የተገለጸው።

መገናኛ ብዙሃን፣ በራሪ ወረቀቶችንና ውይይቶችን በመጠቀም መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱም እንዲሁ።

በድርጊት መርሃ ግብሩ ላይ እንደተመላከተው ትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማትም በግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል።   

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በህገ ወጥ መንገድ ዜጎችን ድንበር የማሻገር ወንጀል በሚፈለገው ደረጃ እየተቃለለ አይደለም፤ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።  

"ኢትዮጵያ በነጻነት የአፍሪካ ኩራት ሆና ብትነሳም ይህ በጎ ገጽታዋ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እየተሸፈነ በመሆኑ በጋራ ሰርቶ ችግሩን ከመሰረቱ መፍታት ይገባል" ብለዋል።  

ኢትዮጵያዊያን በሄዱበት ቦታ ለከፋ ስቃይ፣ እስርና ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ የገለጹት አቶ ደመቀ፣ በሳዑዲ አረቢያ ብቻ 34 ሺህ ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ለማወቅ መቻሉን ጠቅሰዋል።    

እነዚህ ዜጎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በሳምንት አንድ ሺህ ዜጎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።   

"ፈተናውን ለመሻገር ቁልፉ ጉዳይ ህገ ወጥ ዝውውርን ከምንጩ ማድረቅ ነው" ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። 

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሰዎች የተሰወረ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ለመስራት በክልል፣ ወረዳና ቀበሌ ደረጃ ካሉ አካላት ብዙ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።         

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ዜጎች ከሚደርስባቸው እንግልት ለመዳን በህጋዊ መንገድ ብቻ መሄድ ይኖርባቸዋል።

" በሥራ መለወጥ የሚቻለው ውጭ በመሄድ ብቻ ነው የሚለው አመለካከት ሊቀየር ይገባል" ያሉት ሚኒስትሯ፣ የእናቶች እምባ መታበስ እንዳለበት ነው የገለጹት። 

የዜጎች የሥራ ባህል አለመደባር ሌላው ችግር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአገር ውስጥ ሰርተው ድህነትን ከተሻገሩ ሰዎች የስኬት ጉዞ መማር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም