የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ተመሰረተ

103

የካቲት 24/2013 የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ በይፋ ተመሰረተ።

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበርን የመሰረቱት ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ የታሪክ ምሁራን መሆናቸው ተገልጿል።

ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማና አስፈላጊነት አስመልክቶ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር አመራሮች ዛሬ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል።

የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጥጋቡ በዜ ማህበሩ የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶች እንዲታረሙ በአሳማኝ የታሪክ ማስረጃዎች ላይ በመመስረት ሳይንሳዊ የአፃፃፍ ስልትን የተከተሉ የታሪክ ህትመቶች እንዲታተሙ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት የታሪክ ተማራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ የማህበሩ መመስረት የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶች እንዲታረቁ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው ትክክለኛውን ታሪክ ለህዝብ ለማድረስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ዶክተር አለማው ክፍሌ በበኩላቸው ማህበሩ በአገር ግንባታ ሂደትና ብሔራዊ መግባባት ላይ የታሪክ ምሁራን በብቃትና በሙያዊ ስነ ምግባር እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

መረጃን መሰረት ያደረጉ ታሪኮች ለህዝቡ እንዲቀርቡ ከማድረግ ባለፈ ለፖሊሲ ቀራጮች ግብዓት የሚሆኑ ሥራዎችን መስራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚንቀሳቀስም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም