ኢትዮጵያ ሙሉ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር እንዲኖራት እየተሰራ ነው - ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

226

የካቲት 24/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሙሉ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ጄኔራል ብርሃኑ ከተመሰረተ ከ60 ዓመታት በላይ ላስቆጠረው በልዩ ዘመቻዎች ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለሚገነባው አዲስ ሕንጻ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

"አየር ወለድ ለሌላው ሠራዊት ወኔ የሚጨምር የአገሪቷ የክፉ ቀን ደራሽ ነው" ያሉት ጄኔራሉ የልዩ ዘመቻ ኃይል ባልተመቸ ቦታና ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የአየር ኃይል ሠራዊት ማሰልጠኑ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል።

በተለይም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሪፎርም መደረጉን አስታውሰው አሁን በብርጌድ ደረጃ ያለውን አየር ወለድ ወደ ሙሉ ክፍለ ጦር ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህም በአነስተኛ የሰው ኃይል ትላልቅ ግዳጆችን ለመወጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

አየር ወለዱ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት አስፈላጊው መሰረተ ልማት ሊሟላለት ሲገባ ቀደም ሲል በመከላከያ የነበረው አመራር ሆን ብሎ ክፍሉን ሲያዳክመው ነበር ሲሉም ጠቁመዋል።

በዚህም ማሰልጠኛው ለረጅም ጊዜ ሳይታደስ በመቆየቱ መፈራረሱና ለዓይን የማይስብት ገጽታ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

የአገር መከላከያ የሕንጻው ግንባታ እንዲከናወን የወሰነው ክፍሉ ባለው ከፍተኛ ጠቀሜታ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።

አየር ወለድ አገርና ሕዝብ ከጣለበት ኃላፊነት አኳያ ሥራውን በትጋትና በጀግንነት መስራት እንዳለበት ያሳሰቡት ጄኔራል ብርሃኑ፤ "ሰልጣኞች የአገሪቷ የቁርጥ ቀን ሠራዊት መሆናችሁን አስባችሁ በትጋት መስራት ይኖርባችኋል" ብለዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ኃይል የአየር ወለድ ሰልጣኞች በዱከም የዝላይ ሜዳ የአየር ወለድ ዝላይ ትርኢት አሳይተዋል።

የዝላይ ትርኢቱ አየር ወለዱ የደረሰበትን ከፍተኛ አቅም እንደሚያሳይና ሰልጣኞቹም ከአየር ወለድ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የኦፕሬሽናልና የውጊያ ስልጠናዎችን መውሰዳቸው ተነግሯል።

ጄኔራል ብርሃኑና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች የአየር ወለድን የስልጠና ሂደት የጎበኙ ሲሆን ለአየር ወለድ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዲስ ሕንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ሕንጻ በ170 ሚሊዮን ብር  የሚገነባ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሏል።

አየር ኃይል በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ታላላቅ ገድሎችን ያስመዘገበ ሲሆን በቅርቡ በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በናቅፋ 15ኛ ሻለቃን ከጠላት ከበባ ያወጣበት ተጋድሎ ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም