የተለያዩ ተቋማት በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

133
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/11/2010 የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ሰራተኞች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ። የፌዴራል ስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያ የስራ አመራር አባላትና ሰራተኞች፣ የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላኩት መግለጫ በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ህዝባዊ የምክክር መድረክ በኢንጂነሩ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል። የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሶሻል-ዲሞክራቲክ ፓርቲ /ሶኢዴፓ/፣ የቤተመንግስት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብም እንዲሁ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ለኢዜአ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የአገሪቱን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በታማኝነትና በቅንነትና በላቀ ትጋት በመገንባት ባበረከቱት አስተዋጽኦ በታሪክ ሲዘከሩ እንደሚኖሩም ገልፀዋል። የግድቡ ፕሮጀክት በእርሳቸው ህልፈተ-ህይወት እንደማይስተጓጎልና ተጠናቆ ለአገሪቱ የህዳሴ ማረጋገጫ ማህተም እስኪሆን ተቋማቱ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል። የተቋማቱ ሰራተኞች ለኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦቻቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም