በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመግታት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አጥጋቢ ውጤት አልተገኘም - አቶ ደመቀ መኮንን

72

የካቲት 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) “በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመግታት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አጥጋቢ ውጤት አልተገኘም” ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

‘በሰው መነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን መከላከል ባህሉ ያደረገ ህብረተሰብ እንፍጠር’ በሚል መሪ ሀሳብ ብሔራዊ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡መርሃ ግብሩ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም ስራ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፤ በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በደሎች ይፈጸማሉ።

ይህን ችግር ለመግታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም አጥጋቢ ውጤት አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ችግር ለመውጣት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተል በህገወጥ መንገድን የሚደረግ ዝውውርን ከምንጩ ማድረቅና በህግ የተደገፈና በስምምነት ላይ የተመሰረተ መደበኛ የዝውውር መንገድ መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለአገር ውስጥ ስራ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ከአገር ወጥቶ መስራት የሚፈልግ ዜጋ ህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲጠቀም በማስገንዘብ ዜጎችን መታደግ የሚችል ውጤታማ ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው በህገወጥ የሠዎች ዝውውር የሚደርሰው የመብት ጥሰት፣ የአካል ስርቆት፣ የአካል ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ከዚህ አለም አቀፍ ችግር ውጭ ባለመሆኗ በብዙህ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ዜጎች ሕገወጥ ዝውውር ባስከተለው መዘዝ ሰለባ ሆነዋል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም በአገር ውስጥ ላሉ የስራ እድሎች ቅድሚያ መስጠት እና በአገር ውስጥ ሰርተው ስኬታማ የሆኑ ዜጎችን ፈለግ መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዜጎች በሕገወጥ ዝውውር ከሚደርስባቸው አደጋ እንዲጠበቁ ኣሳስበው፤ ከአገር ወጥተው መስራት የሚፈልጉ ደህንነት፣ መብትና ክብርን ማስጠበቅ የሚቻልበት ህጋዊ የስምሪት ሥርዓትን መከተል እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መንገዶች እንዲዘጉና በሰው መነገድ እንዲቆም ህጋዊ መንገድን ለማጠናከር በቅንጅት በመስራት ሁሉም የመፍትሄ አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመግታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራን ማጠናከር፣ ህጋዊ የስራ ስምሪትና የቅንጅት ስራን ማስፋፋት፣ ህጎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በሰው መነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ የማህበረሰብ ውይይት ቡድኖች የእውቅና ሽልማት መሰጠቱን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም