በአድዋ ጀግኖች የተገኘውን ድል በትላልቅ ልማቶችም ላይ ለመድገም አንድነታችን ማጠናከር ይገባል- ከንቲባው

97

ደብር ማርቆስ፤ የካቲት 24/2013 (ኢዜአ) ''የአድዋ ጀግኖች ለሀገራቸውና ባንዲራቸው ክብር ሲሉ ልዩነታቸውን አጥበው በጋራ ታግለው ያገኙትን ድል በትላልቅ ልማቶችም ላይ ለመድገም አንድነታችን ማጠናከር ይገባል'' ሲሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ይትባረክ አወቀ ገለጹ።

125ኛው የአድዋ የድል መታሰቢያ በዓል በደብረማርቆስ ከተማ ንጉስ ተክለሀይማኖት አደባባይ ትናንት በተከበረበት ወቅት ከንቲባው እንዳሉት፤ የአድዋ ድል  ቅድመ አያቶች የጣሊያንን ወራሪ ሃይል በማሸነፍ ለመላው አለም ጥቁሮች ነፃነት ያጎናጸፈ ነው።

የበዓሉ መከበር  የጀግኖች አባቶች  ፈለግ ለመከተል እንደሚያነሳሳ ጠቅሰው፤የብሔር ፖለቲካ ወደ ጎን በመተው በድህነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ በማጠናከር ለብልፅግና መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ትውልዱ የአባቶቹን አደራ የማይበላ የልማት ጀግና እንዲሆን በማድረግ ታሪኩ አይረሴ ሆኖ እንዲያስቀጥል በደብረማርቆስ  በጀግኖች አርበኞች ስም እንዲሰየም  አንድ የመንገድ ፕሮጀክት በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት መጽደቁን አስታውቀዋል።

የአድዋ ጀግኖች ለሀገራቸው ክብር፣ ለህዝባቸውና ባንዴራቸው ከፍታ ሲሉ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ በመቆም ጠላትን ድል እንደነሱት ሁሉ ይህ ትውልድም በህብረት በመታገል በትላልቅ ልማቶች ሃገራዊ ገፅታው ሊቀይር ይገባል ብለዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አቶ አብረሃም አለኽኝ በበኩላቸው  የአድዋ ድል በዓል አፍሪካውያን ስለ መብትና ነፃነታቸው እንዲሟገቱና እንዲያስከብሩ ፈር የቀደደ  መሆኑን ተናግረዋል።

ታሪክ የሌለው ህዝብ የኋላውን እንደማያይ ፤የዛሬውን እንደማይመረምር የነገን መተንበይ የማይችል መሆኑን ጠቅሰው፤ እኛ ግን በአድዋ ድል ታሪካዊ ህዝቦች እንድንሆን ችለናል ብለዋል።

ዛሬ ላይ የውስጥና ውጭ ጠላቶቻችን እየፈጠሩት ያለውን ተግዳሮቶች በመመከት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ትብብርና አንድነት እንደሚያስፈልግ አድዋ አስተማሪ ታሪክ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አባት አርበኛ አቶ ተፈራ ታምሩ በሰጡት አስተያየት የአድዋ ድል አባቶች  የበታችነትን አልቀበልም በማለት የተሰውለት ታሪክ በመሆኑ በደመቀ ሁኔተ መከበሩ ለትውልዱ ኩራት እንዲሰማው የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ዮኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ይኽይስ አረጉ በበኩላቸው አድዋ የአባቶቻችን የአሸናፊነት ልእልና ከፍ አድርጎ ለአለም ማህብረሰብ ያሳየ ነው ብለዋል።

በጦርነቱ ሂደት ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ወጥተው  የተሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰው የአድዋ የድል ታሪክ ወጣቱ ትውልድ ለሀገር አንድነት መከበር ሊጠቀምበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት አመራሮች፣አባት አርበኞች፣ ፈረሰኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም