በሀረና ወረዳ ሁለት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቁ

171

ጎባ፤ የካቲት 24/2013 (ኢዜአ)  በባሌ ዞን ሀረና ወረዳ 12 ሚሊዮን ብር ወጪ ሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቁ።

"እማጅን ዋን ዴይ  " መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት  ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ትምህርት ቤቶቹ  የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻህፍት፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የመምህራን፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያካተቱ መሆናቸውን የዞኑ  ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ናስር አህመድ ገልጸዋል።

ድርጅቱ ግንባታውን ያካሄደው መንግስት  የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ለመሸፈን  እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአርብቶ አደር አካባቢ የተገነቡት ትምህርት ቤቶቹ  የውስጥ ድርጅት ተሟልቶላቸው ሰሞኑን  ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል።

ቀደም ሲል የአርብቶ አደር ልጆች በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት  ባለመኖሩ  ወደ ሩቅ ስፍራ በመሄድ ለመማር ይቸገሩ የነበረው  አሁን በአቅራቢያቸው በመገንባቱ  ተረጋግተው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አስታውቀዋል።

የድርጅቱ ተወካይ አቶ ኡመር ሊሙ  በበኩላቸው ለአገልግሎት ከበቁት በተጨማሪ ድርጅቱ ሁለት ትምህርት ቤቶች በአርብቶ አደሩ አካባቢ  እያስገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም  መንግስት መሰረታዊ የትምህርት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀረና ወረዳ  በካዬ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ሼህ ኡመር ሀሰን በሰጡት አስተያየት  ትምህርት ቤቱ በአካባቢያቸው መገንባቱ ልጆቻቸው በአቅራቢያቸው የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸው ለዚህም  ድርጅቱን አመስግነዋል፡፡

ቀደም ሲል ትምህርት ቤት በአካባቢያቸው ባለመኖሩ  በተለይ ሴቶች ልጆች የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የቡሉቅ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በድሪያ አህመድ ናቸው፡፡

በአካባቢያቸው ተገንብቶ በቅርቡ ለአገልግሎት የበቃው ትምህርት ቤት ልጆቻቸው የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በመደበው ከ118 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ሶስት ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  በዞኑ መደ ወላቡ፣ ሀረና እና ጎሮ ወረዳዎች ውስጥ በመገንባት ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡

በባሌ ዞን ዘንደሮ  ከ400 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ከአንደኛ እስከ  12ኛ ክፍል ተመዝግበው መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውን  ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት  ከተገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም