የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ ዓውደ-ርዕይ ሊካሄድ ነው

78
አዲስ አበባ ሃምሌ 20/2010 የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ ዓውደ-ርዕይ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ዓውደ-ርዕዩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንደሆነና በሚሌኒየም አዳራሽ ነሐሴ 4 እና 5 ቀን 2010 ዓም እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ከደረጃ ዶት ኮም ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት መሆኑን ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በዓውደ-ርዕዩ ከ20 ሺህ በላይ የ2010 ተመራቂ ተማሪዎችና ከ300 በላይ ኩባንያዎች እንደሚገኙ ታውቋል። በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል እንደተናገሩት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ዕቅድ ተነድፎ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ከዩኒቨርስቲ ከሚመረቁ ወጣቶች 80 በመቶ የሚሆኑት በተመረቁ በ12 ወራት በተመረቁበት ሙያ በቅጥር አሊያም በግል ሥራ እንዲሰማሩ የማድረግ ግብ ከዕቅዱ መካከል ይገኝበታል። በአሁኑ ወቅት ተመርቀው ስራ የሚያገኙ ተማሪዎች ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ ከ60 በመቶ እንደማይበልጥ ነው አቶ ደሳለኝ የገለጹት። እስከ 2012 ዓም መጨረሻ ድረስ ቁጥሩን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህ እንዲያግዝም ስራ ፈላጊና አሰሪ ከሚያገናኙ የድረ-ገጽ ተቋማት ጋር ተስማምተን እየሰራን ነው ብለዋል። የደረጃ ዶት ኮም ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ሲሃም አየለ እንዳሉት የዓውደ-ርዕዩ ዋና ዓላማ በ2010 ዓም የተመረቁ ወጣቶች ስራ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸትና ከቀጣሪዎች ጋር እንዲተዋወቁ ማድረግ ነው። በዓውደ-ርዕዩ መሳተፍ የሚችሉት በዚህ ዓመት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች ብቻ ሲሆኑ፤ ምዘገባውን ያለ ክፍያ በደረጃ ዶት ኮም ድረ-ገጽ ማከናወን እንደሚችሉም አስታውቀዋል። እስካሁን አንድ ሺህ ተመራቂዎችን ለመቅጠር ክፍት ቦታ ያላቸው ከ150 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም