ሀገርና ትውልድን በነፃነት ከቆየው የአድዋ ድል ተባብሮ ማደግንም እንደሚቻል የሚያስተምር መሆኑን ወጣቶች ተናገሩ

58

ድሬዳዋ፤ የካቲት 23/2013(ኢዜአ) ፡- ሀገርንና ትውልድን በነፃነት ካቆየው የአድዋ ድል በአብሮነት ተባብሮ ማደግንም እንደሚቻል የሚያስተምር መሆኑን በድሬዳዋ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

የድሬዳዋ ወጣቶች 125ኛ ዓመት የአድዋን ድል መታሰቢያ በዓልን በሚዘክሩ የተለያዩ ትዕይንቶችና ድራማዎች ዛሬ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር በድምቀት አክብረዋል፡፡

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ዳዊት በሽር በተለይ ለኢዜአ እንዳለው፤ የአደዋ ድል ዜጎች በየትኛውም የአለም አደባባዮች አንገታቸውን ቀና አድርገው በነጻነት እንዲኖሩ ያስቻለ ደማቅ ገድል ነው፡፡

ድሉ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት መንገድ የከፈተ ከመሆኑ በሻገር በመተባበርና በመረዳዳት ሀገርን ማሳደግ እንደሚገባ ያስተምራል ብሏል፡፡

የአደዋ ድል ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መስዋዕትነት የከፈሉበት አኩሪ ተግባር መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ወጣት መቅደላዊት እንግዳ ናት፡፡

ድሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን ለድሉ ዋና ምክንያት የሆነው አንድነትን በማጠናከር ሀገርን ለማሳደግ እንድንጠቀምበት የሚስተምረን ነው ብላለች፡፡

ወጣት አረጋ አብደታ በበኩሉ የአድዋ ድል የሰው ልጅ ህልውና መረጋገጥ ህይወት የተገበረበት የኢትዮጵያና የመላው ጥቁር ህዝቦች አኩሪ ታሪክ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ህይወት ከተከፈለለት ድል በመማር መስዋዕት መሆን የማይጠይቀውን ከድሃነት የመውጣትን ዘመቻ ተባብሮና ተረዳድቶ ዳር ማድረስ አለብን ብሏል፡፡

ያለችን አንድ ሀገር ናት፤ ልዩነት አክብረን ያለችንን አገር ወደ ከፍታ መውሰድ አለብን ያለው ደግሞ ወጣት ዮሴፍ ሰለሞን ነው፡፡

የወጣቶቹን የድል ቀን አከባበር ብዛት ያላቸው ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በማጀብ አበረታተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም