የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሠልጣኝ ወጣቶች የአድዋ ድል በዓልን በሠመራ ከተማ በጽዳት ዘመቻ አከበሩ

81

ሠመራ ፤ የካቲት 23/20313(ኢዜአ)  ሠላም ሚኒስቴር በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሚያሠለጥናቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች 125ኛው የአድዋ ድል በዓልን በጽዳት ዘመቻ አከበሩ።

በሠመራ ከተማ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ስራ ከተሳተፉት መካከል ሠልጣኝ ጫሌ ሁሴን በሰጠችው አስተያየት እራሳቸውን ከዘረኝነትና ጥላቻ በማጽዳት በአብሮነትና ፍቅር በዓሉን ከከተማዋ ህብረተሰብ ጋር በማክበሩ መደሰቷን ተናግራለች።

በቀጣይም በህብረተሰቡ ውስጥ በሚኖራቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስምሪትም ልዩነቶችን አቻችለው አብሮነትን፣ ሠላምና ፍቅርን በመስበክ ሀገራዊ አንድነትን  ለማስቀጠል የድርሻውን እንደምትወጣ ገልጻለች።

ታደለች ደነቀ በበኩሏ የአድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያም ብቻም ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀን ነው ብላለች።

ዕለቱን ለአካባቢና ጤና ጠንቅ ከሆኑ ቆሻሻዎችን በማጽዳት ለአብሮነትና አንድነት እንቅፋት ከሆኑ ከፋፋይ አመለካከቶች በመራቅ ጀግኖች አባቶች በአድዋ የተቀዳጁበትን የድል ሚስጥር የሚያስተምሩበትና የሚዘክሩበት ታሪካዊ ቀን መሆኑን ተናግራለች።

በቀጣይ በሚኖረን ማህበራዊ ህይወትም አብሮነትንና መቻቻልን በማስተማር በተለይም እኛ ወጣቶች ትልቅ ትምህርት ልንወስድ  የምንችልበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብላለች።

የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ከራሳቸው ህይወትና ክብር በላይ ለሀገራቸው ሉአላዊነትና ህዝባቸው ደህንነት ዋጋ ከፍለው ነጻነትን ያረጋገጡበት መሆኑን የተናገረው ደግሞ ኡስማን ሁሴን ነው።

በዚህ ታሪካዊ ዕለት ህብረ-ብሄራዊነታችንን ጠብቀን አካባቢያችን በማጽዳት ከቀደምት አባቶቻችን የተረከብናትን ሀገር ከድህነትና ኋላቀርነት ወጥታ ወደ ብልጽግናው ማማ ለማድረስ ሃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ለማሳየትም ጭምር በዓሉን በዚህ መልክ አክብረናል ብሏል።

በሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የሠመራ-ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ያሲን መሐመድ እንደተናገሩት የሠላም ሚኒስቴር በጎ-ፈቃደኛ ወጣቶች የአድዋ ድል በዓልን አስመልክተው በከተማዋ ያደረጉት የጽዳት ስራ የሚበረታታ ነው።

የድል በዓሉ መከበር የአድዋ ጀግኖችን የድል ሚስጥር የሆነውን አብሮነት፣ መተባበርና አንድነት ወደ ትውልዱ በማስረጽ የሀገሪቱን ልማትና እድገት ወደ ከፍታው ማማ ለማቆናጠጥ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።


ወጣቶቹ በዚህ ታሪካዊ ዕለት በዓሉን እራሳቸውን ዝቅ አድርገው ህብረተሰቡን በማገልገል በማሳለፋቸው ከተማ አስተዳደሩ ታላቅ አክብሮትና ምስጋና እንዳለው ገልጸው ይህንን ህብረታቸውን ለቀጣይ ሀገራዊ እድገታችንን ዋስትና መሆኑን ተገንዝበው አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም