ያለ አግባብ የምግብ ሸቀጦችን አከማችተው የተገኙ 197 የነጋዴ መጋዘኖች ታሸጉ

73

ሐረር ፣ የካቲት 23/ 2013(ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ዘይትና የተለያዩ የምግብ ፍጆታቸውን አከማችተው የተገኙ 197 የነጋዴ መጋዘኖች እንዲታሸጉ መደረጉን የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ መሐመድ ዚያድ ከድር እንዳሉት በዞኑ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋለው ህገ ወጥ ተግባር ለመከላከል የፍትህ አካላትና ህብረት ስራ ማህበራት በአባልነት የሚገኙበት ግብረ ሃይል አቋቁመው ወደ ስራ ገብተዋል።

ግብረ ሃይሉ በአንድ ሳምንት ባከናወነው እንቅስቃሴም የምግብ ፍጆታ ሸቀጦችን በድብቅ የማከማቸት እና ያልተገባ የዋጋ መጨመር ህገ ወጥ ድርጊት መታየቱን አስረድተዋል።

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በ197 መጋዘኖችን ውስጥ ዘይት፣ ስኳር፣ዱቄት፣ ሩዝ፣ማካሮኒንና ሌሎች የምግብ ሸቀጦች በህገ ወጥ መንገድ አከማችተው በመገኘታቸው እንዲታሸጉ መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይ በሐረማያ ወረዳ አዴሌ ከተማ በሚገኝ 3 መጋዘኖች ውስጥ ግምቱ 30 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ከ34ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣1ሺህ 850 ኩንታል ሩዝ፣1ሺህ 450 ኩንታል ማካሮኒን፣300 ኩንታል ዱቄትና ሌሎችም የምግብ ሸቀጦች ተከማችተው ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

የታሸጉ መጋዘኖች ባለቤቶች ላይ በአቃቢ ህግ በኩል ክስ በመመስረት ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ያመለከቱት አቶ መሐመድ ዚያድ ህገ ወጥ ተግባር የመቆጣጠርና ገበያውን የማረጋጋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የሐረማያ ወረዳ ንግድ ጽህፈት ቤት የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ ኤልያስ ኡስማን የፍጆታ ሸቀጦችን አለአግባብ በመጋዘን ያከማቹና የተጋነነ ዋጋ በጨመሩ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

በወረዳው የአዴሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሩሚያ አብዲ በሰጡት አስተያየት 150 ብር ይሸጥ የነበረው አምስት ሊትር ዘይት ወደ 400 ብር ኪሎው 25 ብር የነበረው ስኳር 40 ብር በነጋዴው እየተጠየቁ መቸገራቸውን አመልክተው ለማስተካከል መንግስት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአዴሌ ከተማ ነጋዴና የመጋዘን ባለቤት አቶ ሂክንያም ጎሳ እንዳሉት ስንዴ ጠፋ በሚል በተለይ በዱቄት፣ ፓስታና ማካሮኒ ላይ ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል።

እኛም በምናከናውነው የንግድ ስራ ላይ ተጽዕኖ እያደረብን ስለሚገኝ መንግስት በፋብሪካዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም