የአድዋ ድል እሴቶችን በማጎልበት ለሀገር ልማትና ሰላም ግንባታ መትጋት ይገባል-ምሁራን

109

አርባምንጭ/ሆሳዕና የካቲት 23/2013 (ኢዜአ) ከአድዋ ድል ያገኘነውን የመተባበርና የአንድነት እሴት በማጎልበት ለሀገር ልማትና ሰላም ግንባታ ልንተጋ ይገባል ሲሉ የአርባምንጭና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጸ።

125ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በአርባምንጭና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ተከብሯል።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ደርዛ  በወቅቱ እንዳሉት የአደዋ ድል ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት አንድ ሆነው በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ ታሪካዊ ክስተት ነው።

ድሉ የኢትዮጵያዊያን የመተባበርና የአብሮነት መገለጫ እንደሆነም ተናግረዋል።

የአድዋ ድል አብሮነትን፣ ይቻላል ባይነትን፣ በራስ መተማመንና ህብረትን ያጎናጸፈ የጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑንም ገልጸዋል።

የዛሬው ትውልድ ከአድዋ ድል ያገኘውን የአብሮነት፣ የመተባበርና የአንድነት እሴቶች በማጎልበት ለሀገር ልማትና ሰላም ግንባታ  ሊተጋ እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

"ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ወደሚፈለገው ዕድገትና ብልጽግና ለማድረስ ከአባቶቻችን የወረስነውን ትብብርና አንድነት ማጠናከር አለብን " ሲሉ ፕሬዝዳንቱ መክረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዳንኤል ወርቁ በበኩላቸው "ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ከአውሮፓና ከአፍሪካ ሀገራት ገጥሟት የነበረው ወረራና ትንኮሳ የተመከተው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ባደረጉት ትግል ነው" ብለዋል።

ከጣሊያን ጋር በነበረው ጦርነት እቴጌ ጣይቱ ብልህ አመራር በመስጠት በጠላት ጦር ላይ ከበባ በማድረግ የትግል ጊዜውን በማሳጠር የማይተካ ሚና መጫወታቸውን አስረድተዋል፡፡

ሴቶች በማነሳሳትና ለጦርነቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በማድረግ ጣፋጭ ድል እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አውስተዋል።

"አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ክብር አስጠብቀው እንዳቆዩልን ሁሉ ዛሬ ሀገራችንን የሚፈታተኑ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በኢትዮጵያዊ አንድነት ማክሰም ይጠበቅብናል" ብለዋል።

"የአድዋ ድል ጣሊያን በአፍሪካ ለመስፋፋት የቃጣችውን የወረራ ዕቅድ ያጨናገፈ ነው" ያሉት ደግሞ በበዓሉ ላይ በእንግድነት የታደሙት የጋሞ ዞን አባት አርበኞች ማህበር ሰብሳቢ ተስፋዬ ገመዳ ናቸው።

ድሉ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማጽናት ባለፈ በዓለም ዙሪያ ጉልህ ተጽእኖ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በዩኒቨርሲቲው በተከበረው በዓል ላይ እንዳሉት በአድዋ የተገኘውን ድል በመጠበቅ በልማትና በሰላም ላይ በመድገም ደማቅ ታሪክ መጻፍ ይገባል።

"በዘመናዊ መሳሪያ ተደራጅቶ የመጣውን የጣሊያን ጦር በታላቅ የአርበኝነት ድል መምታት የተቻለው ኢትዮጵያውያን በአንድነት መዝመት በመቻላቸው ነው" ብለዋል።

"ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል እሴቶች በመማር አሁን ላይ የተጋረጠብንን ፈተና በአንድነት በመመከት ሀገሪቱ የጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ሊተጋ ይገባል " ሲሉም መክረዋል ።

ትውልዱ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ በማድረግ የበለጸገች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ በማውረስ እንደ የአድዋ ድል የታሪክ ባለቤት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የዩንቨርስቲው ምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ በበኩላቸው የአድዋ ድል  አባቶቻችን የነጭን የበላይነት ባለመቀበል ኢትዮጵያዊ አልደፈር ባይነትን ያሳዩበትና ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"አባቶቻችን ድሉን የተቀዳጁት በሀገራዊ አመለካከት አንድ ስለነበሩ ነው" ያሉት ዶክተር ጸደቀ አሁን ያለው ትውልድ የራሱን ድል ለማስመዝገብ በትጋት መስራት እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም