በኢንጂነር ስመኘው ሞት ሃዘን ቢሰማንም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ እናደርጋለን - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

64
ሀምሌ 20/2010 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ጥልቅ ሀዘን ቢሰማንም ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ትናንት ማለዳ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ በጥይት ተመተው መሞታቸው ይታወቃል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው የግድቡ ግንባታ ከዳር እስኪደርስ ህዝቡ ድጋፉን ማድረግ እንደሚገባውና እነርሱም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ ሊዲያ ወሰን ተስፋ መቁረጥ የለብንም እርሱን የሚተካ ሰው ማፍራት ይኖርብናል  በትዕግስት ና በጥንካሬ ወደ ፊት እያንዳንዳችን ለሀገራችን ማበርከት አለብን ወጣት ተስፋዬ አለባቸው በበኩሉ እኔ የመንግስት ሰራተኛ ነኝ ከዚህ በፊትም ከደመወዜ እየተቆረጠ ቦንድም እየገዛሁ ነው አሁንም የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ዘይኑ ጀማል ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የፖሊስ አባላት የኢንጂነር ስመኘው አሟሟት ለማጣራት ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።  ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስከረም 3 ቀን 1957 ዓ.ም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ስሙ ማክሰኝት በተባለ ቦታ ነው የተወለዱት። ከ1978 እስከ 1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኮተቤ በሚገኘው ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አገልግለዋል። ከ1991 እስከ 1992 በኢንጂነሪንግ ክፍል በሲቪል ምህንድስና ሰርተዋል። ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን የግልገል ጊቤ ሁለት ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን ሰርተዋል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የኢትዮዽያዊያን የድካም ውጤትና ተስፋ በሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም