ዝቅ ብለን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የሚጠይቀን ወቅት ላይ ነው የምንገኘው - ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

107

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23/2013 (ኢዜአ ) የምንገኘው ዝቅ ብለን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የሚጠይቀን ወቅት ላይ ነው ሲሉ የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ለዘላቂ ሠላም ግንባታ ስራው ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ገልፀዋል።

ሚኒስትሯ "በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ" በሚል ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ብሔራዊ የምክክር መድረክ መጠናቀቁን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው አድዋ በየጊዜው ተመንዝረው የማያልቁ ጥልቅና ረቂቅ ምስጢሮች ያሉት የድል በዓል መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ፍትህ ፈላጊ ሕዝቦች ካበረከተቻቸው ስጦታዎች አንዱና ዋነኛው መሆኑን በመጥቀስ።

"አድዋ ከበዓልነት ባሻገር ለመላ ኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለዓለም የጽናት፣ የጥንካሬና የአንድነት መለያ የሆነ ደማቅ ታሪክ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአድዋ ድል አንዱ ምስጢር ሕብረ-ብሔራዊነት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ አሁን ያለንበት ምዕራፍ አስቸጋሪ ቢሆንም ላለፉት ጉዳዮች ሁሉ ይቅር ተባብሎ አብሮነትን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

በአድዋ ድል ሕብረ ብሔራዊነት ችግር እንዳልሆነ በተጨባጭ የታየበት መሆኑን አስታውሰው "ዝቅ ብለን ኢትዮጵያን ወደላይ ከፍ ማድረግ የሚጠይቀን ወቅት ላይ ነው የምንገኘው" ያሉት።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ለዘላቂ ሠላም ግንባታ ሥራው ወሳኝ ሚና አለው።

ዜጎች በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ከቻሉ የአገር ግንባታ ሥራው ደረጃ በደረጃ የሚከወን መሆኑን አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወያዩበትን የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ለሦስት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የሚታዩ ተመሳሳይ ችግሮች ተለይተው የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበውበታል።

ይህም ሚኒስቴሩ በሁለተኛና ሦስተኛ ምዕራፍ ለሚያከናውናቸው የሠላም ግንባታ ሥራዎች የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በመድረኩ ሀሳቦች በነጻነት የተነሱ ሲሆን እንዲህ አይነቱ ውይይት እየዳበረ መምጣት በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት።

በምክክር መድረኩ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከ250 በላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም