በአገራዊ ምርጫው የሠላምና የደህንነት ስጋት እንዳይፈጠር ፓርቲዎች በጋራ መስራት አለባቸው

64

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23/2013 ( ኢዜአ) በመጪው አገራዊ ምርጫ የሠላምና የደህንነት ስጋት እንዳይፈጠር ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ መስራት እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ምርጫው ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሃላፊነቱ ለአንድ አካል የሚተው አለመሆኑን ተናግረዋል።

በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

'ሁሉም ፓርቲዎች ደጋፊና ተቃዋሚ አላቸው' የሚሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ መሪ ወይዘሮ ቆንጂት ብርሃን፤ ሁሉም ፓርቲ በሆደ ሰፊነትና በመቻቻል ሠላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው ብለዋል።

በመቻቻልና በመከባበር ኢትዮጵያን ወደተሻለ ነገ እንድትጓዝ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግዛቸው አመራ በበኩላቸው በአገሪቷ የሚከሰቱ የሠላምና ደህንነት ስጋቶችን የማስቀረት ድርሻው የገዥው መንግስት ብቻ አይደለም ይላሉ።

ይልቁንስ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚደግፋቸውን ሕዝብ የማስተማር ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የሚከሰቱ ችግሮችን አጉልቶ ከማሳየት ይልቅ ለመፍትሄ መዘጋጀት የተሻለ አማራጭ ነው ያሉት ደግሞ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወይዘሮ ነቢሃ ሙሃመድ ናቸው።

ሠላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሁሉም ፓርቲዎች በሃሳብ ላይ የተመረኮዘ ውይይት በማካሄድና ከመጠላለፍ ሴራ በመውጣት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም የፓርቲዎቹ አመራሮች አመልክተዋል።

ግንቦት 28 እንደሚካሔድ ቀን ለተቆረጠለት አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ እያከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም