ጀግኖች አርበኞች ያቆዩልንን ሉአላዊት ሀገር ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል-ምሁራን

88

ሚዛን፣ የካቲት 23/2013 (ኢዜአ ) ጀግኖች አርበኞች በአድዋ ድል ያቆዩልንን ሉዓላዊት ሀገር ጠብቆ ለትውልድ ማሸጋገር እንደሚገባ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ እየተከበረ ያለውን 125ኛው የአድዋ ድል በማስመልከት ምሁራኑ ለኢዜአ እንደገለጹት የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የማንነት አሻራ ያረፈበት ታሪካዊ ክስተት ነው።

ድሉ የዜጎች የመተሳሰብና የአብሮነት እሴት ነጸብራቅ በመሆኑ ለትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የዩንቨርስቲው የታሪክ መምህር አጥናፉ ምትኩ እንደገለጹት "በርሊን ላይ ተካሂዶ በነበረው የአውሮፓውያን  የአፍሪካ ሀገራትን ተቀራምቶ ቅኝ የመግዛት ስምምነት ኢትዮጵያ ለጣሊያን ደርሳ ነበር " ብለዋል።

"ስምምነቱን ተከትሎ ኢጣሊያ ቅኝ ለመግዛት ወይም ለወረራ ምቹ የሚያደርጉ ስምምነት የማዘጋጀት ተግባር ላይ ተሰማርታለች" ያሉት የታርክ ምሁሩ  የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ 17ን  ኢትዮጵያዊያን ባለ መቀበላቸው ወደ ጦርነት መገባቱን አስታውሰዋል።

"በጦርነቱ ጣሊያኖች የጦር የበላይነት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያውያን አርበኞች የሞራልና የሀገር ፍቅር የበላይነት ስለነበራቸው በድል ተወጥተው ዓለምን እንዳስደመሙ ገልጸዋል።

ያኔ በአካባቢ ገዢዎች መካከል ስምምነት አልነበረም፤ ነገር ግን ሀገርን ለመውረር የመጣን የውጭ ኃይል ለመመከት የውስጥ ችግሮችን ወደ ጎን በመተው ከአራቱም አቅጣጫ ያለ ምንም ልዩነት በጋራ ተሰልፈው ድል ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

"ዛሬም በአባይና የህዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ እንዲሁም የሀገር የሉአላዊነት በሚነኩ ጉዳዮች ላይ እንደ አድዋ ሁሉ በህብረት መቆም ያስፈልጋል" ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

"የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ባህልና እሴቱን ይዞ እንዲቆይ ያደረገ ነው" ያሉት መምህሩ ቅኝ የተገዙ የአፍሪካ ሀገራት ማንነታቸው ተደበላልቆባቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን አብራርተዋል።

"ኢትዮጵያውያን መልካም ታሪክና የአሸናፊነት መንፈስ ያለን ነን፤ ታሪካችንን ጠብቆ ለማስቀጠል አድዋ የሞራል ስንቅ ይሆነናል" ያሉት ደግሞ በዩንቨርስቲው የታሪክና ፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ዶክተር ንጉስ በላይ ናቸው።

"አሁን ያለው ትውልድ ከሚያለያዩ ይልቅ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በመተባበር ጀግኖች አርበኞች ያቆሟትን የሁላችንም አምድ የሆነች ኢትዮጵያን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል ።

ከ125 ዓመት በፊት ከነበረው አሁን ላይ የተለየ ነገር አለ " ያለት ምሁሩ ዛሬ ላይ የአድዋን ድል ለመድገም ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ ተግቶ በመስራት ከፍታን መቆናጠጥና የሀገር ልዕልና እንዲጎላ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"በአድዋ መገፋፋትን ሳይሆን መዋሀድን፤ ከልዩነት ይልቅ አንድነትና መተባበርን በማንጸባረቅ ጀግኖች ክብርን ተጎናጽፈዋል" ሲሉ አውስተዋል።

ምሁሩ አክለው "መከፋፈልና መጠላላት ፍጻሜው ሊሆን የሚችለው ውርደት በመሆኑ ከአድዋ ጀግኖች የተረከብናትን ሉአላዊት ሀገር ጠብቀን ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

ጥንታዊ ጀግኖች የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ 17ን አስተውሎ በመመልከት ኢትዮጵያን ከቅኝ አገዛዝ ታድገው ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር እንዳደረጓት ሁሉ ዛሬም በነገሮች ሁሉ ማስተዋልን ልምድ አድርጎ ችግሮችን መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ምሁሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም