ሴቶች በዘንድሮ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል... ሴት መምህራን

55

ጎባ፤የካቲት 23/2013 /ኢዜአ/ ሴቶች በዘንድሮ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ በዴሞክራሲና በሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን ገለጹ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን በዘንድሮ 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ሴቶች በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂደዋል።

ባለፉት ዓመታት ሴቶች በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተሳትፎአቸው ዝቅተኛ እንደነበር መምህራኑ ተናግረዋል።

ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በዘንድሮ  ሀገራዊ ምርጫ  በንቃት በመሳተፍ በሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።  

ከኢዜአ  ጋር ቆይታ ካደረጉት የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን መካከል ወይዘሪት ሄልዲያና ሱሌይማን እንዳሉት የሀገሪቱ ህዝብ ግማሽ አካል የሆኑ ሴቶችን ያላከተተ የትኛውም የልማት ውጥን ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የለውጡ መንግስት ለሴቶች በሰጠው ትኩረት ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት መሳተፍን ጨምሮ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጦች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ መምጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ሴቶችን የሚያሳትፍና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ አውዶችን በመፍጠር በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ውጥኖች ትርጉም ባለው መልኩ ከግብ እንዲደርሱ ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

መምህር ኤልዲያና አክለውም ሴቶችም በሀገሪቱ እየተፈጠሩ በሚገኙ መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም በተለይ በዘንድሮ 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ የዴሞክራሲና የሀገር ግንባታ ሂደቱ አካል መሆን እዳለባቸው መክረዋል፡፡

መንግስት ከሴቶች ተሳትፎ ውጪ ሀገርን መገንባት አዳጋች እንደሆነ በመረዳት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተግባር የሚያረጋግጡ መመሪያዎች በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሰሚራ ናሲር ናቸው፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ሰሚራ እንዳሉት ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን  በመጠቀም በዘንድሮ ምርጫ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ ሊዲያ ትኩ በበኩላቸው ሴቶች በሀገሪቱ ግማሹን የህዝብ ቁጥር እንደመያዘቸው መጠን በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ ሰፊ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም