በጋምቤላ ከተማ 12 ህገ ወጥ ክላሽንኮቭ ጠብ መንጃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ 12 ህገ ወጥ ክላሽንኮቭ ጠብ መንጃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
58
ጋምቤላ ፣የካቲት 23/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኙ 12 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ለኢዜአ እንደገለጹት የጦር መሳሪያዎቹን ትላንት በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለው ከብሐራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ነው።
የጦር መሳሪዎቹ የተገኙት በታንከር ውስጥ ተሸሽገው እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች መካከል ዘጠኝ ታጣፊ እና ሶስት ባለሰደፍ ክላሽንኮቭ ጠብ መንጃዎች ይገኙበታል።
መሳሪያዎቹ በመኖሪያ ቤቱ የተገኘበት ተጠርጣሪ ለጊዜው ቢያመልጥም በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በክልሉ እየተስፋፋ ያለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየሰሩ መሆናቸውን ኮሚሽር አቡላ ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት በተደረገው ጥረት የአሁኖቹን ጨምሮ 329 የክላሽንኮቭና የብሬን ጠብ መንጃዎች እንዲሁም 2ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።