የአድዋ ድል መንፈስን እስከተላበስን ድረስ በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ችግሮች መፍታት አይሳነንም ...ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

44

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/ 2013 (ኢዜአ) “የአድዋ ድል መንፈስን እስከተላበስን ድረስ በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት የሚሳነን አይሆንም” ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክትር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላትና ሌሎችም ጥሪ ተደረገላቸው እንግዶቸና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።

በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ “የአድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦችን ቅኝ ግዛትና ባርነትን ከመጣል የሚያግዳቸው ምድራዊ ሃይል እንደሌለና የኢትዮጵያውያን ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው” ብለዋል።

“የአድዋ ድል ምንጊዜም ሁል ጊዜም አዲስ ነው የድሉ መንፈስ ለማናቸውም የሰው ልጆች የህይወት መመሪያ ሆኖ እስከ ዘላለም የሚዘልቅ መሆኑ ጥርጥር የለውም ነው” ያሉት።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ዘላለማዊ ታሪክ ጽፈው የሚያልፉ ኩሩ ህዝቦች መሆናቸውን ያሳዩበትም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

“አባቶቻችን በአድዋ ያሳዩት አንድነትና መተሳሰብ፣ ጽናትና አይበገሬነት፣ ለኢትዮጵያ የነበራቸው ፍቅርና ታማኝነት ነው’ ይህንን ለዘላለም ማጽናት ይኖርብናል” ብለዋል።

የአድዋ ድል መንፈስን እስከተላበስን ድረስ በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት የሚሳነን አይሆንም በማለትም አመለክተዋል።

“ኢትዮጵያ ከፖለቲካና ማናቸውም ልዩነት በላይ መሆኗን አባቶቻችን እንዳሳዩን ሁሉ ሁሉም ነገር ከኢትዮጵያ በታች መሆኑን አይተን ለአገራችን ሰላምና ልማት በጋራ መቆም ይኖርብናል” ብለዋል።

“ችግሮቻችንን በቅጡ ለይተን መፍትሔ በመፈለግ ወደ ነገ ልንሻገር ይገባል” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ እርስ በርስ መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንቷ “ተግዳሮቶቻችንን ቀንሰን ደስታችን እንዲበዛ ለአገራችን ክብርና እድገት በጋራ እንሰለፍ” ብለዋል።

የ21ኛ ክፍለ ዘመን የክተት ጥሪም አገራችንን በጋራ ተግተን እናሳድግ የሚል ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም