ኀብረቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚያራምዱትን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ አስታወቀ

67
አዲስ አበባ ሃምሌ 20/2010 የአውሮፓ ኅብረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚያራምዱትን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ አስታወቀ። በኢትዮጵያ የኅብረቱ ልዑክ መሪ አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በሚወስዷቸው የለውጥ እርምጃዎች አማካኝነት የታዩትን ለውጦች ኅብረቱ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ኅብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል። የኀብረቱ አባል አገሮችም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሰብዓዊ መብት አከባበር ላይ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየታቸውን የገለጹት አምባሳደር ጆሃን፤ አሁንም በአገሪቷ የተጀመረውን ለውጥ ለመደገፍ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሚደነቅና ለቀጣናው ሰላም መስፈን ከማስቻሉም በላይ ለአፍሪካ አገሮችና ለመላው ዓለም ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሠላም ለአብነት ያነሱት አምባሳደር ጆሃን፤ በፊት ከነበሩበት የጠላትነት እንቅስቃሴ "በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሠላም መምጣታቸው የሚደነቅና የአለምን ህዝብ የሚያነሳሳ ነው" ብለዋል። የዓለም ህዝብ በአገሮቹ መካከል የተደረሰውን የሠላም ስምምነት በመደገፍ የተጀመረው ግንኙነት በጠንካራ የኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማገዝ ሰፊ ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል። በአገሪቷ ያለውን የፖሊቲካ ምህዳር ለማስፋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ሁሉንም የሚያግባባና እርቅ የሚያወርዱ መሆኑን አብራርተዋል። የአውሮፓ ኀብረት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርጉ አጋሮች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከአገሪቷ ጋር በንግድ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በቀጣናዊ ሠላምና ደህንነት እንዲሁም በስደተኞች ጉዳዮች በጋራ የሚሰራ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም