ከቀጣዩ በጀት ዓመት ጀምሮ አዋጭነታቸው ያልተረጋገጠ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች በጀት አይመደብላቸውም - የገንዘብ ሚኒስቴር

104

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2013 ( ኢዜአ) ከቀጣዩ በጀት ዓመት ጀምሮ አዋጭነታቸው ያልተረጋገጠ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች በጀት እንደማይመደብላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የግዥ ስርዓቱን ማዘመን ዓላማ ያደረገ የግዥ ማሻሻያ አዋጅ መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አዋጭነታቸው ሳይረጋገጥ በጀት የሚመደብላቸው የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ለሐብት ብክነትና ለግንባታ መጓተት መንስኤ መሆናቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

መንግስት ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የፌዴራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር አዋጅ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

በአዋጁ መሰረት በፕላንና ልማት ኮሚሽን ታይቶና ተገምግሞ አዋጭነቱ ያልተረጋገጠ ፕሮጀክት በጀት እንደማይመደብለት በግልጽ ማስቀመጡን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረት መንግስት ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ አዋጭነታቸው ላልተረጋገጠ የልማት ፕሮጀክቶች በጀት መመደብ እንደሚያቆም ነው ያስታወቁት።

የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ መሰረት የተቀመጠላቸውና በግንባታ ላይ የሚገኙ አገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ይህ ተግባራዊ መደረጉ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ከማድረግ አኳያ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።

የገንዘብ ሚኒስቴር በአጠቃላይ ፕሮጀክቶችን መቆጣጠር የሚያስችለውን የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱንና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማን መሰረት በማድረግ ገንዘብ እንደሚለቀቅም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የተንዛዛውን የግዥ ስርዓት እንደሚቀይርና እንደሚያዘምን የታመነበት የግዥ ማሻሻያ አዋጅ መዘጋጀቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።

እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ በኢትዮጵያ ያለው ረጅምና የተንዛዛ የግዥ ስርዓት አገሪቷን ተጠቃሚ ያላደረገና ውጤታማም እንዳልሆነ በመንግስት ተገምግሟል።

ለዚህም የግዥ ስርዓቱን በማዘመን አሁን ያለውን ስርዓት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀይር የታመነበት የግዥ ማሻሻያ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አዋጁ ግዥዎችን በአጭር ጊዜ መከወን የሚያስችልና ትልቅ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በግዥ ጨረታ ሂደት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚያስችሉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን መያዙን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የግዥ ሂደት አነስተኛ አቅም ያላቸው ተቋማት እንዲሳተፉ የሚያደርግ እንደሆነና በተሻሻለው አዋጅ ተጫራቾች የጨረታ ማስያዣ ቦንድ /ቢድ ቦንድ/ እንዲያስይዙ እንደሚያስገድድ ጠቁመዋል።

ይህ መሆኑ ትልቅ አቅም ያላቸው ድርጅቶች በጨረታዎች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የገለጹት።

የግዥ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እየታየ እንደሚገኝና በተያዘው በጀት ጸድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

የውጭ ኩባንያዎች ብቻ እቃ በዱቤ ከውጭ አገር እንዲያስገቡ የሚያደርገውን መመሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያሻሻለው እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እየተሻሻለ ያለው መመሪያ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እቃ በዱቤ ከውጭ አገር እንዲያስገቡ እንደሚፈቅድ ይሄም ባለሀብቶችን ለማበረታት አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው በቅርቡ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር አክለዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ማሻሻያዎች የተደረጉበት የታሪፍ መጽሐፍም ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚካሄድበት ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የታሪፍ መጽሐፍ አምራቹን የማይደግፍ፣ የገቢ ንግድን የሚያበረታታና የቀረጥ ምጣኔውን ምርትና ምርታማነት የማያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መጽሐፉ የነበሩ የአሰራር ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ያስቀመጠና አምራቾችን የሚያተጉ ማበረታቻዎችን እንደያዘም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የታክስና የቀረጥ እፎይታዎችን በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ብቻ እንዲሰጡ የሚያስችል አዋጅ እየዘጋጀ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

ይህ እንዲሆን ያስፈለገበት ምክንያት እፎይታ አሰጣጡ የተሰበሰበ እንዲሆን በማድረግ አሰራሩ ላልተፈለገ ዓላማ እንዳይውል ለማድረግ ነው ብለዋል።

አዋጁ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ በጣም አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የታክስ እፎይታ የሚሰጠው በገንዘብ ሚኒስቴር ብቻ መሆኑንና ማዕድን፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ እፎይታዎች በዘርፉ ባሉ ተቋማት መሰጠት እንደሚቀጥሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም