የመራጮች ምዝገባ ቀን ከየካቲት 22 ወደ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ተዘዋወረ

68

የካቲት 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) የመራጮች ምዝገባ ቀን ከየካቲት 22 ወደ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲዘዋወር መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።

በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ተከታዩ ዋና ተግባር የመራጮች ምዝገባን ማከናወን እንደሆነ የገለጸው ቦርዱ፤ የምርጫ ተግባራትን ማከናወን ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት እንደሆነ ገልጿል።

ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የምርጫ ክልል ቢሮዎች ዝግጅት መዘግየት እንደሆነ ጠቁሟል።

አስፈጻሚዎች ሰልጥነው ከተሰማሩም በኃላ ቢሮዎች ዝግጁ ሆነው ባለመገኘታቸው የእጩዎች ምዝገባ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት መጀመር አለመቻሉ እና ለሁለት ዙር መከፈሉ፣ ለምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት የትራንስፖርት እጥረት እና የገለልተኛ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሂደት ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጊዜ የሚወስድ ተግባር መሆኑን አመልክቷል።

በዚህም መሰረት ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም አራት ተጨማሪ ቀናት በመስጠት የምዝገባ ሂደቱን እንዳራዘመ አስታውሷል።

በሁለተኛ ዙር የእጩዎች ምዝገባ የተጀመረባቸው ክልሎችም ላይ የቢሮዎች ዝግጅት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ችግር ሆኖ እንደነበር መረዳቱን ገልጿል።

የገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ተግባርንም እያከናወነ እንደሆነ የገለጸው ቦርዱ፤ 140 ሺህ በላይ እጩ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚነት የሚሰሩ ግለሰቦችን አዘጋጅቶ ገለልተኝነት የማጣራትን ተግባሩ ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ሊወስድ መቻሉን ጠቁሟል።

በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠመው የቁሳቁስ ማጓጓዝ ተግዳሮቶች በመገምገም እና የእጩ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ስራን በተሻለ ጥራት ለማከናወን የመራጮች ምዝገባን ከተያዘለት ቀን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ መጋቢት 16 ቀን 2013 እንዲዘዋወር መወሰኑን ገልጿል።

በመሆኑም የ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን መሆኑን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም