ለሀገር ግንባታ የጋራ ኃላፊነት ለመወጣት እያገዘ የሚገኘው የባህል ስፖርት ውድድር ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኮሚሽኑ

83

ድሬዳዋ ፤ 22/2013 (ኢዜአ) ዜጎችን በጋራ አሰባስቦና አንድነት ፈጥሮ በሀገር ግንባታ ላይ የተናጠልና የጋራ ኃላፊነት ለመወጣት እያገዘ የሚገኘው የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ውድድር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ፤

 የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ሥነ-ሥርዓት ትናንት ሲካሄድ የኢፌድሪ ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር ዱቤ ጁሎ እንደተናገሩት የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫሉ ብሔር ብሔረሰቦች  የርስ በርስ በመተባበር  አንድነታቸውን  አጽንተው ለሀገር ግንባታና ዕድገት የድርሻቸውን ለመወጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡

ሊጠፋ የደረሱትን የባህል ስፖርቶች ወደ ነበሩበት ለመመለስ መልካም አጋጣሚ እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በባህል ስፖርት ተሣትፎና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው  ይህም ዜጎች በተናጠልና በጋራ በሀገር ደረጃ የተገኘው ለውጥ ለማስቀጠልና አንድነታቸው ለማጠናከር እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

 ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቱና ፌስቲቫሉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች፣ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽንና በየደረጃው የሚገኘው ነዋሪዎች ከየክልሎቹ ለመጡት ተሣታፊዎች  ላደረጉት አቀባበልና ላሳዩት ፍቅር ምክትል ኮሚሽነር ዱቤ አመስግነዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ዝግጅቱ የአድዋ ድል 125ኛ መታሰቢያ በዓል  ጋር መገጣጠሙ  ለባህል ስፖርት ውድድሩና ፌስቲቫሉ ልዩ ድባብ ይፈጥራል ብለዋል ፡፡

ውድድሩንና ፌስቲቫሉ ሲከበር የአድዋ ድልን ያጎናጸፈው አንድነት፣ ወንድማማችነት፣  ሀገራዊ ፍቅርና አይበገሬነትን መውሰድና መተግባር እንደሚገባ ተናግረዋል።

 የአሁኑ ትውልድ የህዳሴ ግድብን ዳር በማድረስ ወደ ብልጽግና ለመጓዝ በሚደረገው ጥረት በመሳተፍ  አዲስና ደማቅ ታሪክ ለመጻፍ መረባረብ እንዳለበት ም አመልከተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል  ህዝቦች ባህላቸውንና  ቱፊቶቻቸውን  የሚለዋወጡበትና የርስ በርስ ግንኙነታቸው የሚያጠናክሩበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ሻኪር አህመድ ናቸው፡፡

"ይህ ደግሞ በሀገር ሰላም፣ ዕድገት፣ ልማት ላይ ተሳትፎን ለማሳደግ ያነቃቃል " ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አስፋው ወቅታዊ ችግር ከገጠመው ከትግራይ በስተቀር ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በውድድሩ ላይ ተካፋይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ውድድር የኮሮና መከላከያ መንገዶችን በመተግበርና በመፈጸም በስፖርታዊ ጨዋነት የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተናጋጅነት የተዘጋጀው 18ኛው የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ውድድርና የ14ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ሲካሄደ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎችና ትዕይንቶች እንዲሁም  ያለፉትን ውድድሮችና ፌስቲቫሎች  የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ  ቀርበዋል፡፡

ለአንድ ሣምንት በሚቆየው ውድድሩ  11  ዓይነት የባህል ስፖርቶች  እንደሚካሄዱ  በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ተገልጿል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም