ለውጡን ከዳር ለማድረስ አንድ ሀገራዊ መግባቢያ ሰነድ ማዘጋጀት ተገቢ ነው---ፕሮፌሰር መድኃኒዬ ታደሰ

88
መቀሌ ሐምሌ 20/2010 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ለውጥ ከዳር ለማድረስ አንድ ሀገራዊ መግባቢያ ሰነድ ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን የፖሊቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር መድኃኒዬ ታደሰ አስታወቁ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ምሁራንን፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር፤ ዓረና ለፍትህና ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ተወካዮች የተሳተፉበት "የትግራይ አስተዳደር ፎረም" በሚል ርዕስ  የተዘጋጀ ፎረም በመቀሌ ተካሄዷል፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኒዬ  ታደሰ በፎረሙ "በኢትዮጵያ አሁን ያለው የፖሊቲካ ኢኮኖሚና የፖሊቲካ አስተዳደር" በሚል ርዕስ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት አሁን ለውጥ የሚፈልግና በተለያዩ አካባቢ ያለውን የፖሊቲከው ተቃርኖውን በማጥበብ ወደ አንድ ቦታ መምጣት አለበት፡፡ ለዚህም  ደግሞ አንድ ሀገራዊ መግባቢያ ሰነድ ቢኖር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖሊቲካ ሽግግር ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ዴሞክራሲዊ ተቋማትን በማጠናከር ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የትግራይ ምሁር የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በተለያዩ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን የፖሊቲካ ምሁሩ፤ ልዩነቱን በማጥበብ ወደ አንድ ሀገራዊ አጀንዳ መምጣት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ "ፎረሙ ያለ ገደብ ሀሳብ የተንሸራሸረበትና ለውጥ የሚፈልግ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል" ያሉት ደግሞ የትግራይ ዴሞክራሲ ትብብር  ክፍተኛ አመራር ኢንጅነር ግደይ ዘርአጽዮን ናቸው፡፡ ከ40 ዓመታት በውጭ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ቤት መግባታቸው ኢህአደግ ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን እንደሚያመልክት ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ አብረሃ ሃይለዝጊ በፎሮሙ ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት የሚጠቅሙ በርካታ ሀሳቦች የቀረቡበት መሆኑን  ገልጿል፡፡ በፎረሙ ወቅት የተገኙት የትግራይ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል  ፎረሙ ለክልሉና ለሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ሀሳቦች የተንሸራሸሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "ፎሮሙ  በቀጣይ  ባለሙያዎችን ጨምሮ ለአንድ የውይይት መድረክ የሚቀርቡ የመወያያ አጀንዳዎች ውስን ቢሆኑም ይበልጥ ጥልቀትና ጠቀሜታ ይኖራቸዋል" ብለዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም