የአድዋ ድል የአፍሪካ አገራት ለነፃነታቸው እንዲታገሉ በር የከፈተ ነው

63

የካቲት 21/2013 (ኢዜአ) የአድዋ ድል የቅኝ ግዛት ቀንበር የወደቀባቸው የአፍሪካ አገራት ለነፃነታቸው እንዲተጉና ቅኝ ገዢዎችን እንዲታገሉ በር የከፈተ መሆኑ ይገለጻል።

የአህጉሪቱ ዜጎች ከአድዋ ድል አንድነትን በመማርና ልዩነትን በመተው በጋራ የተሻለች አህጉር ለመፍጠር ሊተጉ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አፍሪካዊያን ተናግረዋል።

የዛሬ 125 አመት ኢትዮጵያዊያን የኢጣልያን ጦር በማሸነፍ በአድዋ የተጎናፀፉት ድል ለመላው አፍሪካ መነሳሳትን የፈጠረና ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳየ ነው።

በወቅቱ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው ሲዘምቱ ኢጣልያ ግዛቷን ለማስፋፋት ኢትዮጵያን ብትወርም በጀግኖች እምቢ ባይነት ሽንፈትን ተከናንባለች።

በአድዋ ድል የተነቃቃው አፍሪካዊ ለነፃነቱ እንዲነሳ ድሉ መሰረት ሆኖታል።  

በኢትዮጵያ የናሚቢያ አምባሳደር ኢማሊያ ሙኩሳ እንዳሉት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ካስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር ሌሎች የአፍሪካ አገራት ቅኝ ግዥዎችን እንዲዋጉ በር የከፈተ ነው።

የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከልና መቆጣጠር ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ስቴፈን ጆካ እንደተናገሩት የአድዋ ድል የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ራሳቸውን እንዲያላቅቁ ትምህርት የሰጠ ነው።

የጋምቢያ ወታደራዊ አታሼ ሪል አድሚራል ሳጆ ፎፉና በበኩላቸው የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ታሪክ ነው ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የአፍሪካ አገራት ከአድዋ ድል የአንድነትን ኃይል በመማር አህጉሪቱን ወደ እድገት ማምጣትና ልዩነትን ጥንካሬ አድርጎ መጓዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

መለያየት ወደኋላ የሚጎትት እንደሆነ ለትውልድ ማስተማር ይገባልም ነው ያሉት።

የአድዋ ድል 125ኛ ዓመት በዓል ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ በ"የህብረ ብሔራዊ አንድነት ዓርማ " በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም