የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ

71

የካቲት 21/2013 (ኢዜአ)ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ስብሰባ የዳኞችና የተለያዩ ሀላፊዎችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።

ጨፌው በዛሬ ውሎው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን 158 ዳኞችን ሹመት አፅድቋል።

በዚህም መሰረት 11 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ 43 የከፍተኛ ፍርድቤት ዳኞች እና 104 የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፅድቋል።

ሹመቱ በክልሉ ያለውን የፍርድ ሂደት ቀልጣፋ ያደርገዋል ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ አቶ ነመራ ቡሊ የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሀላፊ፣ አቶ ጌቱ ወዬሶ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ሀላፊ፣ ወይዘሮ ሰአዳ ኡስማን የኦሮሚያ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም አቶ ሁሴን ኡስማን የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመሆን ተሹመዋል።

ተሿሚዎቹ ቃለመሀላ ፈፅመዋል።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ የስራ ዘመን 6ኛ አመት 13ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ አዋጆችን በማፅደቅ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም