ወጣቱ ትውልድ የአደዋን ድል በልማት ሊደግም ይገባል -ርእሰ መሰተዳደር አወል አርባ

85

ሰማራ የካቲት 21/2013 (ኢዜአ) አባቶቻችን በአደዋ ድል የሀገራችዉን ሉአላዊነት ለማስከበር የሠሩትን አኩሪ ታሪክ ወጣቱ በልማት ሊደግመው ይገባል ሲሉ አፋር ክልል ርእሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስገነዘቡ።

125ኛው የአደዋ ድል በአል በአፋር ክልል ደረጃ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተከብሯል።

የከልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በወቅቱ እንደገለጹት የአደዋ ድል አፍሪካን ጥሬ ሃብቷን  ሲቀራመቱ ከነበሩ የዘመናት የነጮች የበላይነት አስተሳሰብና ታሪክ ያስቀየረ ነው።

በድሉ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተሳተፉበትና መዋእትነት የከፈሉበት በመሆኑ ሁሉም ሊኮራበት የሚገባ የጋራ ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል።

የአደዋ ድል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ድል ብቻም ሳይሆን ከሰው ሳይቆጠሩ አሰከፊ የጭቆና ቀንበር ተጭኗቸዉ ሲጨቆኑ ለኖሩ አፍሪካዉያንና የመላው ጥቁር ህዝቦችየተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ድል መሆኑን አመልክተዋል።

የአሁኑ ትውልድ የድሉን ታሪክ  በአግባቡ ተረድቶ አንድነቱን በማጠናከር በልማት ሊደግመው እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"የአድዋ ድል የምንኮራበት ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ ችግሮቻችንን እየፈታን እድነታችንንና ልማታችንን ልናስቀጥልበት የሚገባን እርሾ ነው" ብለዋል ርእሰ መሰተዳደሩ።

"በዚህ ወቅት ጀግንነት ማለት ተዋግቶ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን  እውቀትና ክህሎት ታጥቆ ቀን ከሌት ጠንክሮ በመስራት  ሀገርንና ትውልድን ከድህነት በማውጣት ድል መንሳት ነው" ሲሉም ተናግረዋል ።

ዛሬም ሀገራችን ከአደዋ ያልተናነሱ ታሪክ ለሚሠራበት የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንቅፋት የሚሆኑ የውስጥና የውጭ ስጋቶችን በአንድነት በመጋፈጥ የአባቶችን አኩሪ ታሪክ በልማት መድገም እንደሚገባ አስገንዘበዋል። 

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ አሊ መሀመድ በበኩላቸው "የአፋር ህዝብ በአደዋ ጦርነት ብቻም ሳይሆን ከበዛም ቀደም ብሎ ከግብጽና ፈረንሳይ እንዲሁም ከሌሎች ቀኝ ገዢዎች ጋር በመዋጋት የሀገሩን ሉአላዊነት ሳያስደፍር ድንበር እየጠበቀ የኖረ ህዝብ ነው" ብለዋል።

ህዝቡ አኩሪ ታሪኩን  አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ሀገረመንግስት ግንባታና ብልጽግና  የሚፈልገውን ሁሉ በማድረግ  ለመድገም ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል ።

በበአሉ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት አባቶች፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በአደዋ ድል የኢትዮጵያውያን አኩሪ ገድልና የአፋር ህዝብ ተሳትፎን የሚሳይ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም