"ኢትዮጵያዊያን የወገናቸው ህመም ሊያማቸው ይገባል"-- ታማኝ በየነ

60

የካቲት 21/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን የወገናቸው ህመም ሊያማቸው፤ ችግሩን ችግሬ ብለው ሊደርሱለት ይገባል" ሲል አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ገለጸ።

ባለሀብቶች፣ግለሰቦችና ተቋማት በትግራይና መተከል ለሚገኙ ዜጎች ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

"ሰብአዊነትና ፍቅር፣ለትግራይና ለመተከል" በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በነበረው ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋናና የእውቅና መርሃ-ግብር ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በትግራይ ክልል በሕግ ማስከበር እርምጃው እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በንጹሃን ዜጎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይታወቃል።

በጣይቱ ሆቴል ከየካቲት 2 እስከ የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት(ግሎባል አሊያንስ)፣ የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ማህበር፣ የትግራይና መተከል እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመተባበር ድጋፉን ሲያሰባስቡ ቆይተዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብ፣የምግብ፣የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት(ግሎባል አሊያንስ) ሊቀ-መንበር አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ የድጋፍ ማሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን ለወገናቸው ተቆርቋሪ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩበት ነው ብሏል።

ድጋፉ ሲጀመር ለወገን ችግር ደራሽ የመሆኑን አላማ ማሳካቱን ገልጿል።

ኢትየጵያዊያን የወገናቸው ህመም ሊያማቸው ይገባል ያለው ታማኝ በችግር ላይ የወደቁ ወገኖችን መርዳት እንዳለበት ገልጾ ወገን ለወገኑ የሚደርስ ከሆነ ኢትዮጵያን ማቆየት እንደሚቻል ተናግሯል።

በጎፈንድሚ በውጭ ካለው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንና በአገር ውስጥም እስካሁን ድረስ ያልተጠቃለለ ከሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጿል።

ምሽቱን በነበረው የምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ በነበረበው የድጋፍ ቃል ማስገቢያ ስነ ስርዓትም ባለሀብቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ተጨማሪ ከዘጠኝ ነጥብ ሶሰት ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በትግራይና በመተከል ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የትግራይ እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪ ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረጻዲቅ በድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት ልግስና ማንነታቸው የሆነ ደግ ልቦችን ማየቷን ትገልጻለች።

የኢትዮጵያዊያን የመረዳዳት ባህል መንፈስ ከፖለቲካ ሁኔታና ማንነት ያለፈ መሆኑን መረዳት መቻሏን ተናግራለች።

በወቅቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስነ-ስርዓቱ ተካፋዮች በበኩላቸው ሰብአዊነት ከፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ጎሳና ብሔር ያለፈ የሰውነት መገለጫ መሆኑንና ኢትዮጵያዊያንም ይሄን በመረዳት ለወገናቸው በመድረስ አለኝታነታቸውን ማሳየት ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከሚያለያዩ ነገሮች የሚያስተሳስሯቸው በርካታ መሆናቸውን በመግለጽ በሚያዛምዱ ጉዳዮች በጋራ በመቆም እርስ በእርስ በመረዳዳት ችግሮችን መሻገር ይገባል ብለዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ለወገናቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በምስጋና መርሃ ግብሩ በሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ የተዘጋጀ ስዕል ለጨረታ ቀርቦ በ400 ሺህ ብር ተሸጧል።

"ሰብአዊነትና ፍቅር፣ለትግራይና ለመተከል" በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በነበረው ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

የተሰባሰበው ድጋፍ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አማካኝነት እንደሚሰራጭና ስርጭቱን አስመልከቶ የሚከናወኑ ስራዎች ዛሬ እንደሚጀመሩ በመርሃ ግብሩ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም