ከጋምቤላ ለገበታ ሀገር ልማት ፕሮጀክቶች ከ30 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

71

ጋምቤላ የካቲት 21 /2013 ዓም (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ለገበታ ሀገር ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከ30 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የክልሉ ፋይናንሰና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

 በክልሉ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የተጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቢሮው ገልጿል።

 የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደገለጹት እንደ ክልል ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ ለመሰብሰብ ከታቀደው 44 ሚሊየን ብር እስካሁን ከ30 ሚሊዮን 730 ሺህ  ብሩ ተሰብስቧል ።

ድጋፉ የጎርጎራ፣ የወንጪና የኮይሻ የገበታ ለሀገር ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል ።

ድጋፉ ከክልል እስከ ወረዳ ከሚገኙ ከሁሉም  የመንግስት አመራሮችና  ሰራተኞች  የተሰበሰበ  መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ባለህብቶችን፣ የንግዱ ማህበረሰቡንና ሌሎች ነዋሪዎችን  በማሳተፍ በክልሉ  ለመሰብሰብ የታቀደውን ገቢ ለማሳካት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ፕሮጀክቶቹ የህዝቦችን አንድነትና ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን  በማሳደግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገትና የብልጽግና ጉዞ መፋጠን አስተዋጻቸው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ።

ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድም ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹን በህዝቦች ተሳተፎ የመገንባት ሂደቱ ጋምቤላን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመሳሳይ ሁኔታ ለማልማት ተነሳሽነትን የሚፈጥር  ጭምር መሆኑን አስታውቀዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም