በደቡብ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አፍራሽ ተግባራት ሊቆሙ ይገባል--- የክልሉ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

72
ሀወሳ ሐምሌ 20/2010 በደቡብ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አፍራሽ ተግባራት ተገቢነት የሌላቸው በመሆኑ ሊቆሙ እንደሚገባ የክልሉ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ "የምናለማት እንጂ የምናጠፋት አገር የለችንም" በሚል ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ሁከትና ረብሻዎች ተጨማሪ የህይወት ጥፋት፣ የንብረት ውድመትና የዜጎችን መፈናቀል እያስከተሉ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል። በቅርቡ በካፋ፣ በየም፣ በኮንታ፣ በስልጤና ትላንት ደግሞ በሳውላ የታዩት ኃይል የተሞላባቸው ሁከቶች ተገቢነት የሌላቸው መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫው በጥፋትና በውድመት የሚያተርፍ አካል ባለመኖሩ በጥፋቶቹ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ አሳስቧል። "የሰዎች ሕይወትን አደጋ ላይ በመጣልና ንብረት በማውደም ፍላጎትን ለመግለጽ መሞከር ፈጽሞ የህዝቡ እሴት አይደለም " ያለው መግለጫው  ጥያቄ ሲኖር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚቻል አስታውቅል። በአካባቢዎቹ እየተስተዋለ ያለው ድርጊት ለዓመታት የተገነባውን ሰላምና እየተረጋገጠ ያለውን ልማት ወደኋላ የሚጎትት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ከንደዚህ አይነት ድርጊት ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቋል፡፡ የሰላሙ ባለቤት የሆነው የክልሉ ህዝብ በየአካባቢው ተመሳሳይ ድርጊቶች ሲያጋጥሙት በንቃት መከታተልና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት በመስራት ሊከላከል እንደሚገባም መግለጫው አመልክታል። የክልሉ መንግስት የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ መሆኑንም መግለጫው አያይዞ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም