ሞሪንጋ ተክል ለመድሀኒትነት እንደሚውል በምርምር ተረጋገጠ -- ኢንስቲትዩቱ

524

አርባምንጭ የካቲት 21/2013 (ኢዜአ) ሞሪንጋ እንዲሁም ሽፈራው እየተባለ የሚጠራው ተክል ለተለያዩ በሽታዎች ለመድሃኒትነት መዋል እንደሚችል በምርምር መረጋገጡን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በሞሪንጋ ዙሪያ በተደረጉ የምርምር ስራዎች ዙሪያ የሚመክር መድረክ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የኢኒስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ እንደገለጹት ኢኒስቲትዩቱ የማህበረሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሟላት በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የአስር አመት መሪ ዕቅድ በማውጣት ወደ ስራ ገብቷል።

“ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም ባህላዊ መድሀኒቶችን በዘመናዊና ሳይንሳዊ ጥናቶች ለመደገፍ የትኩረት አቅጣጫ በማደረግ ከሀገር ውስጥና አለም ዓቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርጋቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ጉልህ ስፍራ አላቸው" ብለዋል።

ኢኒስቲቲውቱ ካተኮረባቸው መካከል ሞሪንጋ ለህብረተሰቡ ደህንነት ደረጃውን የጠበቀ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ሞሪንጋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ ትኩረትን እየሳበ የመጣና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሀገር በቀል እጸዋት መሆኑን ተናግረዋል ።

እጽዋቱ ለመድሀኒትነት ያለውን ፋይዳ በምርምርና ጥናት በመለየት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪና የሞሪንጋ ምርምር ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር አስፋው ደበላ በበኩላቸው በምርምሩ የጤና፣ ስነምግብ፣ የግብርና፣ የትምህርትና ሌሎች 13 ተቋማት ተሳታፊ ሆነውበታል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች የምርምር ተቋማት ከሀያ ዓመት በላይ በሞሪንጋ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ቢደረግም ከሳይንሳዊ ህትመት ያለፈ ፋይዳ እንዳልነረው አስታወሰዋል።።

ላለፉት ሶስት ዓመታት የማህበረሰቡን ዕውቀት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት ጥቅም ላይ ለማዋል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

"በምርምሩ የሞረንጋ ቅጠል፣ ፍሬውና ግንዱ ለመድሀኒትነት፣ ጨዋማ መሬትን ለማከምና ለሌሎች ተግባራት መዋል እንደሚችል ተረጋግጧል" ያሉት ዶክተር አስፋው ሶስት አዲስ ግኝት እንዳለና የዕውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሞሪንጋ መድሀኒት እንደሚሆን ከተረጋገጠባቸው በሽታዎች መካከል ስኳርና ደም ብዛትን ጠቅሰዋል።

በባህላዊና ዘመናዊ የምርምር ዳይሬክቶሬት ተባባሪ ተመራማሪ ወይዘሪት ጽዮን ካሳሁን እንዳሉት ምርምሩ በርካታ አካላትን ያሳተፈ ውጤትም ያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ሞሪንጋን ለተለያዩ በሽታዎች መከላከያ እንደመድሀኒት ይጠቀምበት እንደነበር ተመራማሪዋ አስታውሰው ከምጣኔና አጠቃቀም አንጻር ያለውን ክፍተት መሰረት ባደረገ መልኩ በዘመናዊ መንገድ የማዘጋጀት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ በሞሪንጋ ዙሪያ የተደረጉ 11 የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን ለተመራማሪዎችም ዕውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም