ወጣቱ ትውልድ ለአንድነትና ለጋራ ሃገር ዋጋ መክፈልን ከአድዋ ጀግኖች ሊማር እንደሚገባ ተገለጸ

81

ደብረብርሃንና ባህርዳር  የካቲት 21/2013 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ አንድነትንና ለጋራ ሃገር እስከ መስዋዕትነት መታገልን ከአድዋ ጀግኖች መማር እንዳለበት ተገለጸ።

በደብረብርሃንና ባህርዳር ከተሞች የአድዋ ጀግኖችን የሚዘክር የእግር ጉዞና የሩጫ ውድድር ተካሒዷል።

ዛሬ ረፋድ ላይ በባህርዳር በተካሔደው የዕግር ጉዞ ላይ የተሳተፉት የከተማው ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ አበባ ከሀሊ እንደገለጹት "ጉዞ ለጣይቱ" በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የእግር ጉዞ ዓላማ የአድዋ ጀግኖችን ገድል ለማሰብ ነው።

ሁለት ኪሎ ሜትሮችን በሸፈነው ጉዞ ላይ ከከተማዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የሴት አደረጃጀቶችና አመራሮች የተሳተፉበት የእግር ጉዞው ወራሪውን ጦር በመደምሰሱ ሂደት ዕትጌ ጣይቱ የሰጡትን በሳል አመራር የሚዘክር መሆኑንም ጠቁመዋል።

"በዓሉን ስናክብር እኛ ሴቶች ያገኘነውን ፖለቲካዊ ነጻነት ተጠቅመን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሚክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ንቁ ተሳትፎ መድረግ አለብን" ብለዋል።

በተመሳሳይም በደብረብርሃን ከተማ እለቱን በማሰብ ከ50 ሺህ በላይ ተሳታፊ በተካፈለበት የ8 ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ታየ እንደተናገሩት መድረኩ ወጣቱን ለሃገር ሰላም፣ ለህዝቦች መፈቃቀርና አንድነት ድርሻ እንዲወጣ የሚያነቃቃ ነው።

"ኩራ በሚኒሊክ፤ ኩሪ በጣይቱ" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ውድድር ላይ በአድዋ ድል የብሄራዊ አንድነታችን አርማ ነው የሚል መልዕክት የተላለፈበት መሆኑንም ተናግረዋል።

"የአድዋን በዓል በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማጀብ ታላቅ የቱሪስት መስህብ ማድረግ ይቻላል" ያሉት ደግሞ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ትእግስት መኳንንቴ ናቸው።

ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል አንድነትንና ጀግንነትን በመማር የእርስ በእርስ ግጭትና መጠላለፍን በማስወገድ ለአገር እድገት፣ ብልጽግናና ሉአላዊነት መከበር በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በእለቱ በተካሄደው የሩጫ ውድድርም አትሌት ተሾመ ወንድወሰን፣ መንገሻ ጸጋየና ንጋቱ ጥላሁን ከአንድ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በእለቱም ከጅሩ መገንጠያ እስእንቁላል ኮሶ ያለዉ 8 ኪሎ ሜትር ጎዳና በአፄ ሚኒሊክ፣ ከአየማን መናፈሻ ጅሩ መገንጠያ በፊታዉራሪ ገብርየና የአንኮበር መገጠያ ተብሎ የሚጠራዉ አደባባይ በንጉስ ሳህለ ስላሴ ተሰይሟል።

ከዚህ በተጨማሪም የጅሩ መገጠያ አደባባይ ደግሞ በባልቻ አባነፍሶ የተሰየመ ሲሆን የደብረ ብርሀን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእቴጌ ጣይቱ ስም ተሰይሟል።

ዝክረ አድዋ ድል 125ኛ በዓል በባህርዳር ከተማ ከየካቲት 19/2013 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እስከ የካቲት 23/2013 ዓ.ም ድረስ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም